የሉቃስ ወንጌል 17
17
ስለ ጥፋት መምጣት
1ጌታችን ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፥ “መሰናክል ግድ ይመጣል፤ ነገር ግን መሰናክልን ለሚያመጣት ሰው ወዮለት። 2ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ አህያ የሚፈጭበት የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም በተሻለው ነበር። 3#ማቴ. 18፥15። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወንድምህ አንተን ቢበድል ብቻህን ምከረው፤ ቢጸጸት ግን ይቅር በለው። 4በየቀኑ ሰባት ጊዜ ቢበድልም ሰባት ጊዜ ከተጸጸተ ይቅር በለው።”
ስለ ሃይማኖት ኀይል
5ሐዋርያትም ጌታን፥ “እምነትን ጨምርልን” አሉት። 6ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ብትኖራችሁ ይህችን ሾላ ከሥርሽ ተነቅለሽ በባሕር ውስጥ ተተከዪ ብትሉአት ትታዘዝላችኋለች።”
ስለ መታዘዝ
7“አራሽ ወይም ከብት ጠባቂ አገልጋይ ያለው ከእናንተ ማን ነው? ከእርሻው በተመለሰ ጊዜ ጌታው ና፥ ፈጥነህ ወደዚህ ውጣና ከእኔ ጋር በማዕድ ተቀመጥ ይለዋልን? 8እራቴን አዘጋጅልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስም ታጥቀህ አሳልፍልኝ፤ ከዚህም በኋላ አንተ ብላ፥ ጠጣም ይለው የለምን? 9እንግዲህ ጌታው ያዘዘውን ሥራውን ቢሠራ ለዚያ አገልጋይ ምስጋና አለውን? 10እንዲሁ እናንተም ያዘዝኋችሁን ሁሉ አድርጋችሁ ‘እኛ ሥራ ፈቶች አገልጋዮች ነን፤ ለመሥራትም የሚገባንን ሠራን’ በሉ።”
ዐሥሩን ለምጻሞች እንዳነጻ
11ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ዐለፈ። 12ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች ተቀበሉትና ራቅ ብለው ቆሙ። 13ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ እዘንልን” አሉ። 14#ዘሌ. 14፥1-32። ባያቸውም ጊዜ፥ “ወደ ካህን ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ” አላቸው፤ ሲሄዱም ነጹ። 15ከእነርሱም አንዱ እንደ ነጻ ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ቃል እያመሰገነ ተመለሰ። 16በግንባሩም ወድቆ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና አመሰገነው፤ ሰውየውም ሳምራዊ ነበር። 17ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የነጹ ዐሥር አልነበሩምን? እንግዲህ ዘጠኙ የት አሉ? 18ወገኑ ሌላ ከሆነ ከዚህ ሰው በቀር ለእነዚያ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገን ተሳናቸውን?” 19እርሱንም፥ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው።
ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መምጣት
20ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ጠየቁት፤ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም። 21እንኋት፥ በዚህ ናት፤ ወይም እነኋት፥ በዚያ ናት አይሉአትም፤ የእግዚአብሔር መንግሥትስ እነኋት፥ በመካከላችሁ ናት።”
22ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፥ “ከሰው ልጆች ቀኖች አንዲቱን ታዩ ዘንድ የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩአትም። 23እነሆ፥ በዚህ ነው፥ ወይም እነሆ፥ በዚያ ነው ቢሉአችሁ አትውጡ፤ አትከተሉአቸውም። 24መብረቅ ብልጭ ብሎ ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ እንደሚያበራ የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ነውና። 25ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ብዙ መከራን ይቀበላል፤ ይህች ትውልድም ትንቀዋለች፤ ትፈታተነዋለችም። 26#ዘፍ. 6፥5-8። በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ እንዲሁ ይሆናል። 27#ዘፍ. 7፥6-24። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡ ነበረ፤ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን አንድ አድርጎ አጠፋ። 28በሎጥ ዘመንም ሲበሉና ሲጠጡ፥ ቤት ሲሠሩና ተክል ሲተክሉ፥ ሲሸጡና ሲገዙ ነበረ። 29#ዘፍ. 18፥20—19፥25። ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነመ፤ ሁሉንም አጠፋ። 30የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ አይታወቅምም። 31#ማቴ. 24፥17-18፤ ማር. 13፥15-16። ያንጊዜም በሰገነት ላይ ያለ፥ ገንዘቡም በምድር ቤት የሆነበት ሰው ለመውሰድ አይውረድ፤ በዱር ያለም ወደ ኋላው አይመለስ። 32#ዘፍ. 19፥26። የሎጥን ሚስት ዐስቡአት። 33#ማቴ. 10፥39፤ 16፥25፤ ማር. 8፥35፤ ሉቃ. 9፥24፤ ዮሐ. 12፥25። ነፍሱን ሊያድናት የሚወድ ይጣላት፤ ስለ እኔ#“ስለ እኔ” የሚለው በግሪኩ የለም። ነፍሱን የሚጥላትም ያድናታል። 34እላችኋለሁ፦ ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይተኛሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ። 35ሁለት ሴቶችም በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዪቱንም ይተዋሉ። 36ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ላይ ይኖራሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ።” 37እነርሱም መልሰው፥ “አቤቱ፥ ወዴት ነው?” አሉት፤ እርሱም፥ “ገደላ በአለበት አሞሮች በዚያ ይሰበሰባሉ” አላቸው።
Právě zvoleno:
የሉቃስ ወንጌል 17: አማ2000
Zvýraznění
Sdílet
Kopírovat
Chceš mít své zvýrazněné verše uložené na všech zařízeních? Zaregistruj se nebo se přihlas