የሉቃስ ወንጌል 1
1
ወንጌልን ስለ መጻፍ
1በእኛ ዘንድ የተፈጸመውንና የታመነውን የሥራውን ዜና በሥርዐት ሊጽፉ የጀመሩ ብዙዎች ናቸው። 2ከእኛ አስቀድሞ በዐይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩ እንደ አስተላለፉልን፤ 3የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው ተከትዬ፥ ሁሉንም በየተራው እውነተኛውን እጽፍልህ ዘንድ መልካም ሁኖ ታየኝ። 4የተማርኸውን የነገሩን እውነት ጠንቅቀህ ታውቅ ዘንድ።
ስለ ዘካርያስና ስለ ኤልሳቤጥ
5 #
1ዜ.መ. 24፥10። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። 6ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በእግዚአብሔር ሥርዐትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ነበሩ። 7ልጅም አልነበራቸውም፤ ኤልሳቤጥ መካን ነበረችና፤ ሁለቱም አርጅተው ነበር፤ ዘመናቸውም አልፎ ነበር።
8እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በተራው የክህነትን ሥራ በሚሠራበት ጊዜ፥ 9ካህናት እንደሚያደርጉት የሚያጥንበት ጊዜ ደረሰ፤#በግሪኩ “ዕጣ ደረሰው” ይላል። ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ። 10ዕጣን በሚያጥንበት ጊዜም ሕዝቡ በሙሉ በውጭ ይጸልዩ ነበር። 11የእግዚአብሔር መልአክም በዕጣን መሠውያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው። 12ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ ፍርሀትም ረዓድም ወረደበት። 13መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቶአልና፤ ሚስትህ ኤልሣቤጥም ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። 14ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። 15#ዘኍ. 6፥3። እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ ሁሉ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል። 16ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ይመልሳቸዋል። 17#ሚል. 4፥5-6። እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓድያንንም ዐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ፥ ሕዝብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኀይል በፊቱ ይሄዳል።” 18ዘካርያስም የእግዚአብሔርን መልአክ እንዲህ አለው፥ “ይህ እንደሚሆን በምን አውቃለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅችአለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል።” 19#ዳን. 8፥16፤ 9፥21። መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ። 20አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኽኝምና ይህ እስኪሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም ይሳንሃል።” 21ሕዝቡ ግን ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ዘግይቶ ነበርና እጅግ ተደነቁ። 22ወደ እነርሱ ወደ ውጭ በወጣ ጊዜም እነርሱን ማነጋገር ተሳነው፤ በቤተ መቅደስም የተገለጠለት እንዳለ ዐወቁ፤ እንዲሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያመለከታቸው ኖረ። 23ከዚህም በኋላ የማገልገሉ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ።
24ከእነዚያም ቀኖች በኋላ#አንዳንድ የግእዝ ትርጕም “ከሁለት ቀኖች በኋላ” ይላል። ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ፅንስዋንም ለአምስት ወር ሸሸገች፤ እንዲህ ስትል፦ 25“እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ በጐበኘኝ ጊዜ እንዲህ አደረገልኝ።”
ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን እንደ አበሠራት
26በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስሟ ናዝሬት ወደምትባለው ወደ አንዲት የገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሚሆን ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨችው ወደ አንዲት ድንግል ተላከ፤ 27#ማቴ. 1፥18። የዚያችም ድንግል ስምዋ ማርያም ይባል ነበረ። 28መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፥ “ደስ ያለሽ፥#“ደስ ያለሽ” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። ጸጋንም የተመላሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት። 29እርስዋም በአየችው ጊዜ ከአነጋገሩ የተነሣ ደነገጠችና “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?” ብላ ዐሰበች። 30መልአኩም እንዲህ አላት፥ “ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ። 31#ማቴ. 1፥21። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። 32እርሱም ታላቅ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። 33#2ሳሙ. 7፥12-13፤ 16፤ ኢሳ. 9፥7። ለያዕቆብ ወገንም ለዘለዓለሙ ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” 34ማርያምም መልአኩን፥ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል?” አለችው። 35መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፥ “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል፤ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል። 36እነሆ፥ ከዘመዶችሽ ወገን የምትሆን ኤልሣቤጥም እርስዋ እንኳ በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ፀንሳለች፤ መካን ትባል የነበረችው ከፀነሰች እነሆ፥ ይህ ስድስተኛ ወር ነው። 37#ዘፍ. 18፥14። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና”። 38ማርያምም መልአኩን፥ “እነሆኝ፥ የእግዚአብሔር ባሪያው አለሁ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለችው፤ ከዚህ በኋላም መልአኩ ከእርስዋ ዘንድ ሄደ።
ማርያም ወደ ኤልሣቤጥ ስለ መሄድዋ
39በዚያም ወራት ማርያም ፈጥና ተነሣች፤ ወደ ተራራማው ሀገር#ግእዙ “ደወለ ዐይነ ከርም” ይላል። ወደ ይሁዳ ከተማም ደረሰች። 40ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሣቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። 41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ዘለለ፤ በኤልሣቤጥም መንፈስ ቅዱስ መላባት። 42በታላቅ ቃልም ጮሃ እንዲህ አለች፥ “ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው። 43የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ? 44እነሆ፥ ሰላምታ ስትሰጭኝ ቃልሽን በሰማሁ ጊዜ፥ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። 45ከእግዚአብሔር ዘንድ የነገሩሽ ቃል እንደሚሆን የምታምኚ አንቺ ብፅዕት ነሽ።”#በግሪኩ “ከእግዚአብሔር የተነገረላት ይፈጸማልና የምታምን ብፅዕት ናት” ይላል።
46 #
1ሳሙ. 2፥1-10። ማርያምም እንዲህ አለች፥ “ሰውነቴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች። 47ልቡናዬም በአምላኬ በመድኀኒቴ ሐሤት ታደርጋለች። 48#1ሳሙ. 1፥11። የባርያውን ትሕትና ተመልክቶአልና። እነሆ፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል። 49ታላቅ ሥራን ሠርቶልኛልና፤#በግሪኩ “ብርቱ የሆነ እርሱ ለእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና” ይላል። ስሙም ቅዱስ ነው። 50ይቅርታውም ለሚፈሩት ለልጅ ልጅ ነው። 51በክንዱ ኀይልን አደረገ፤ በልባቸው ዐሳብ የሚታበዩትንም በተናቸው። 52#ኢዮብ 5፥11፤ 12፥19። ኀያላኑን ከዙፋናቸው አዋረዳቸው፤ ትሑታኑንም ከፍ ከፍ አደረጋቸው። 53የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው፤ ባለጠጎችንም ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው። 54ብላቴናውን እስራኤልን ተቀበለው፤ ይቅርታውንም ዐሰበ። 55#ዘፍ. 17፥7። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ እስከ ዘለዓለም እንደ ተናገረው።”
56ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚህ በኋላም ወደ ቤቷ ተመለሰች።
ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ልደት
57የኤልሣቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። 58ዘመዶችዋና ጎረቤቶችዋም እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። 59#ዘሌ. 12፥3። ከዚህም በኋላ በስምንተኛው ቀን ሕፃኑን ሊገዝሩት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። 60እናቱ ግን መልሳ፥ “አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ” አለች። 61እነርሱም፥ “ከዘመዶችሽ ስሙ እንደዚህ የሚባል የለም” አሉአት። 62አባቱንም ጠቅሰው፥ “ማን ሊሉት ትወዳለህ?” አሉት። 63ብራናም ለመነና “ስሙ ዮሐንስ ይባል” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም አደነቁ። 64ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተናገረ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ። 65በዚያም ሀገር ሰው ሁሉ ላይ ፍርሀት ሆነ፤ ይህም ነገር ሁሉ በይሁዳ በተራራማው ሀገር ሁሉ ተወራ። 66የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና።
67በአባቱ በዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ መላበት፤ እንዲህም ብሎ ትንቢት ተናገረ፦ 68“ይቅር ያለን፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ 69ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤ 70ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን በነቢያት አፍ እንደ ተናገረ። 71ከጠላቶቻችን እጅ፥ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ። 72ቸርነቱን ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ፥ ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ። 73ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ያስብ ዘንድ። 74ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሀት፥ 75በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ በዘመናችን ሁሉ እንድናመልከው ይሰጠን ዘንድ። 76#ሚል. 3፥1። አንተም ሕፃን፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ትጠርግ ዘንድ በፊቱ ትሄዳለህና። 77ኀጢአታቸው ይሰረይላቸው ዘንድ መድኀኒታቸውን እንዲያውቁ ለአሕዛብ ትሰጣቸው ዘንድ። 78ከአርያም በጐበኘን በአምላካችን በይቅርታውና በቸርነቱ። 79በጨለማና በሞት ጥላ ለነበሩት ብርሃኑን ያሳያቸው ዘንድ፥ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም ጎዳና ያቀና ዘንድ ወጣ።” 80ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸና፤ ለእስራኤልም እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።
Právě zvoleno:
የሉቃስ ወንጌል 1: አማ2000
Zvýraznění
Sdílet
Kopírovat
Chceš mít své zvýrazněné verše uložené na všech zařízeních? Zaregistruj se nebo se přihlas