የዮሐንስ ወንጌል 1
1
ቃል ሥጋ ሆነ
1በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። 2እርሱ በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። 3ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የሆነ የለም። 4በእርሱ ሕይወት ነበረች፤ ሕይወትም የሰዎች ብርሃን ነበረች። 5ብርሃንም በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም።
6 #
ማቴ. 3፥1፤ ማር. 1፥4፤ ሉቃ. 3፥1፤2። ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ 7እርሱ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፤ ሁሉም በእርሱ በኩል ያምኑ ዘንድ። 8ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።
9ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር። 10በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለም ግን አላወቀውም። 11የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። 12ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበትን ሥልጣን ሰጣቸው፤ 13እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።
14ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በእኛም ዘንድ አደረ፤ ጸጋንና እውነትን የተመላውን፥ የአባቱ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብሩንም አየን። 15ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፤ እንዲህም ብሎ ጮኸ “‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤’ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።” 16እኛ ሁላችንም ከሙላቱ ተቀበልን፥ በጸጋ ላይ ጸጋን፤ 17ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። 18እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ገለጠው።
የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት
(ማቴ. 3፥1-12፤ ማር. 1፥1-8፤ ሉቃ. 3፥1-18)
19አይሁድም “አንተ ማን ነህ?” ብለው ለመጠየቅ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። 20መሰከረም፤ አልካደምም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ መሰከረ። 21#ሚል. 4፥5፤ ዘዳ. 18፥15፤18፤ ሲራ. 48፥10፤11።“እንግዲያውስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ብለው ጠየቁት። “አይደለሁም” አለ። “ነቢዩ ነህን?” “አይደለሁም” ብሎ መለሰ። 22“እንግዲያውስ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። 23#ኢሳ. 40፥3።እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ።
24የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩ፤ 25“እንግዲያውስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። 26ዮሐንስ መልሶ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ 27ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የተገበሁ አይደለሁም” አላቸው። 28ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር።
የእግዚአብሔር በግ
29በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። 30‘አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይበልጣል፤’ ብዬ ስለ እርሱ የተናገርሁት ይህ ነው። 31እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁት።” 32ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ “መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይም ሲኖር አየሁ። 33እኔም አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ ‘መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው፤’ አለኝ። 34እኔም አይቻለሁ፥ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ።”
የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት
35በማግሥቱ ዮሐንስ ከሁለት ደቀመዛሙርቱ ጋር እንደገና እዚያ ቆሞ ነበር፤ 36ኢየሱስንም ሲራመድ ተመልክቶ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ፤” አለ። 37ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። 38ኢየሱስም መለስ ብሎ ሲከተሉትም አይቶ “ምን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ረቢ!፥ (ሲተረጎም ‘መምህር ሆይ’ ማለት ነው) የምትኖረው የት ነው?” አሉት፤ 39እርሱም “መጥታችሁ እዩ፤” አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፤ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ ጊዜው ወደ ዐሥር ሰዓት ገደማ ነበር። 40ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። 41እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና “መሢሕን አግኝተናል” አለው፤ ትርጓሜውም “ክርስቶስ” ማለት ነው። 42ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ” አለው፤ ትርጓሜውም “ጴጥሮስ” ማለት ነው።
የፊልጶስ እና የናትናኤል መጠራት
43በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ” አለው። 44ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። 45ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በሕግ#1፥45 በኦሪት መጻሕፍት ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል፤” አለው። 46ናትናኤልም “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” አለው። ፊልጶስ “መጥተህ እይ” አለው። 47ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ “ተንኰል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው እነሆ!” አለ። 48ናትናኤልም “እንዴት አወቅኸኝ?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ፥ አየሁህ፤” አለው። 49ናትናኤልም መልሶ “መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው። 50ኢየሱስም መልሶ “ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ፤” ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው። 51#ዘፍ. 28፥12።“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።
Právě zvoleno:
የዮሐንስ ወንጌል 1: መቅካእኤ
Zvýraznění
Sdílet
Kopírovat
Chceš mít své zvýrazněné verše uložené na všech zařízeních? Zaregistruj se nebo se přihlas