ትንቢተ ኢዩኤል 1
1
1ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2እናንተ ሽማግሌዎች፥ ይህን ስሙ፥ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፥ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን? 3ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፥ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፥ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ። 4ከተምች የቀረውን አንበጣ በላው፥ ከአንበጣም የቀረውን ደጎብያ በላው፥ ከደጎብያም የቀረውን ኩብኩባ በላው።
5በተሃ ወይን ጠጃችሁ ከአፋችሁ ተወግዶአልና እናንተ ሰካራሞች፥ ነቅታችሁ አልቅሱ፥ እናንተም የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ፥ ዋይ በሉ። 6ቍጥርም የሌለው ብርቱ ሕዝብ በምድሬ ላይ ወጥቶአልና፥ ጥርሳቸው እንደ አንበሳ ጥርስ፥ መንጋጋቸውም እንደ እንስቲቱ አንበሳ መንጋጋ ነው። 7ወይኔን ባዶ ምድር አደረገው፥ በለሴንም ሰበረው፥ ባዶም አደረገው፥ ጣለውም፥ ቅርንጫፎቹም ነጡ።
8ለቍንጅናዋ ባል ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ድንግል አልቅሺ። 9የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከእግዚአብሔር ቤት ተወግዶአል፥ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናቱ አለቀሱ። 10እህሉ ጠፍቶአልና፥ ወይኑም ደርቆአልና፥ ዘይቱም ጐድሎአልና እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአል፥ ምድሪቱም አልቅሳለች። 11መከሩ ከእርሻቸው ጠፍቶአልና ገበሬዎች ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ አፈሩ፥ የወይን አትክልተኞችም አለቀሱ። 12ወይኑ ደርቆአል፥ በለሱም ጠውልጎአል፥ ሮማኑና ተምሩ እንኰዩም የምድርም ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፥ ደስታም ከሰው ልጆች ዘንድ ርቆአል።
13የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከአምላካችሁ ቤት ቀርቶአልና እናንተ ካህናት፥ ማቅ ታጥቃችሁ አልቅሱ፥ እናንተም የመሠዊያ አገልጋዬች፥ ዋይ በሉ፥ እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች፥ ኑ፥ ሌሊቱን ሁሉ በማቅ ላይ ተኙ። 14ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ።
15የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል። 16ከዓይናችን ፊት ምግብ፥ ከአምላካችንም ቤት ደስታና እልልታ የጠፋ አይደለምን? 17ዘሩ በምድር ውስጥ በሰበሰ፥ እህሉ ደርቆአልና ጎተራዎቹ ባዶ ናቸው፥ ጎታዎቹም ፈርሰዋል። 18እንስሶች እጅግ ጮኹ፥ የላምም መንጎች ማሰማርያ የላቸውምና ተጠራጠሩ፥ የበግም መንጎች ጠፍተዋል። 19አቤቱ፥ እሳት የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና፥ ነበልባሉም የዱሩን ዛፍ ሁሉ አቃጥሎአልና ወደ አንተ እጮኻለሁ። 20ፈሳሹ ውኃ ደርቆአልና፥ እሳቱም የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና የምድር አራዊት ወደ አንተ አለኸለኹ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢዩኤል 1: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in