መጽሐፈ ኢዮብ 32
32
1ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ሰዎች መመለስን ተዉ። 2ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቍጣ ነደደ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው። 3ደግሞም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ። 4ኤሊሁ ግን ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ከኢዮብ ጋር መናገርን ጠብቆ ነበር። 5ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ።
6የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ እንዲህም አለ፦
እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፥
ስለዚህም ሰጋሁ፥ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ።
7እንደዚህም አልሁ፦ ዓመታት በተናገሩ ነበር፥
የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር።
8ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥
ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል።
9በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥
ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም።
10ስለዚህም፦ ስሙኝ፥
እኔ ደግሞ እውቀቴን እገልጥላችኋለሁ አልሁ።
11እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥
የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ
ብልሃታችሁን አዳመጥሁ።
12እንዲሁም ልብ አደረግሁ፥
እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥
ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም።
13እናንተም፦ ጥበብን አግኝተናል፥
እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ።
14እርሱ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልተናገረም፥
እኔም በንግግራችሁ አልመልስለትም።
15እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም፥
የሚናገሩትንም አጡ።
16እነርሱ አልተናገሩምና፥
ቆመው ዳግመኛ አልመለሱምና እኔ በትዕግሥት እጠብቃለሁን?
17እኔ ደግሞ ፈንታዬን እመልሳለሁ፥
እውቀቴንም እገልጣለሁ፥
18እኔ ቃል ተሞልቻለሁና፥
በውስጤም ያለ መንፈስ አስገድዶኛልና።
19በተሐ ጠጅ እንደ ተሞላና ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥
ሊፈነዳ እንደማይችል እንደ ወይን ጠጅ
አቁማዳ፥ እነሆ፥ አንጀቴ ሆነ።
20ጥቂት እንድተነፍስ እናገራለሁ፥
ከንፈሬን ገልጬ እመልሳለሁ።
21ለሰው ፊት ግን አላደላም፥
ሰውንም አላቈላምጥም።
22በማቈላመጥ እናገር ዘንድ አላውቅምና፥
ያለዚያስ ፈጣሪዬ ፈጥኖ ከሕይወቴ ይለየኝ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 32: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in