YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢዮብ 31

31
1ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥
እንግዲህስ ቈንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?
2የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ከላይ፥
ሁሉንም የሚችል አምላክ ርስት ከአርያም ምንድር ነው?
3መዓትስ ለኃጢአተኛ፥
መለየትስ ለሚበድሉ አይደለችምን?
4መንገዴን አያይምን?
እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?
5-6በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥
እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ።
በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ
እግሬም ለሽንገላ ቸኵላ እንደ ሆነ፥
7እርምጃዬ ከመንገድ ፈቀቅ ብሎ፥
ልቤም ዓይኔን ተከትሎ፥
ነውርም ከእጄ ጋር ተጣብቆ እንደ ሆነ፥
8እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፥
የሚበቅለውም ሁሉ ይነቀል።
9ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደ ሆነ፥
በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ፥
10ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥
ሌሎችም በእርስዋ ላይ ይጐንበሱ።
11ይህ ክፉ አበሳ፥
ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፥
12ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥
ቡቃያዬንም ሁሉ የሚነቅል ነውና።
13ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥
ሙግታቸውን ንቄ እንደ ሆነ፥
14እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ?
በጐበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታልሁ?
15እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን?
በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለንምን?
16ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፥
የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥
17እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥
ድሀ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፥
18እርሱን ግን ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥
እርስዋንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፥
19ራቁቱን የሆነው ሰው ሲጠፋ፥
ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን አይቼ እንደ ሆነ፥
20ጐንና ጐኑ ያልባረከችኝ፥
በበጎቼም ጠጕር ያልሞቀ እንደ ሆነ፥
21በበሩ ረዳት ስላየሁ፥
በድሀ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፥
22ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፥
ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር።
23የእግዚአብሔር መዓት አስደንግጦኛልና፥
በክብሩም ፊት ምንም ለማድረግ አልቻልሁም።
24ወርቅን ተስፋ አድርጌ፥
ጥሩውንም ወርቅ፦ በአንተ እታመናለሁ ብዬ እንደ ሆነ፥
25ሀብቴ ስለ በዛ፥
እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፥
26ፀሐይ ሲበራ
ጨረቃም በክብር ስትሄድ አይቼ፥
27ልቤ በስውር ተታልሎ፥
አፌም እጄን ስሞ እንደ ሆነ፥
28ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና
ይህ ደግሞ ፈራጆች የሚቀጡበት በደል በሆነ ነበር።
29በሚጠላኝ መጥፋት ደስ ብሎኝ
ክፉ ነገርም ባገኘው ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፥
30ነገር ግን በመርገም ነፍሱን በመሻት
አንደበቴን ኃጢአት ይሠራ ዘንድ አልሰጠሁም፥
31በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች፦
በከብቱ ሥጋ ያልጠገበ ማን ይገኛል? ብለው እንደ ሆነ፥
32መጻተኛው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥
ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር፥
33በደሌንም በብብቴ በመሸሸግ
ኃጢአቴን እንደ ሰው ሰውሬ እንደ ሆነ፥
34ከሕዝብ ብዛት ፈርቼ፥
የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥
ዝም ብዬ ከደጅ ያልወጣሁ እንደ ሆነ፥
35የሚያዳምጠኝ ምነው በኖረልኝ!
እነሆ የእጄ ምልክት፥
ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፥
ከባላጋራዬ የተጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ!
36በትከሻዬ ላይ እሸከመው፥
አክሊልም አድርጌ በራሴ አስረው ነበር፥
37የእርምጃዬን ቍጥር አስታውቀው፥
እንደ አለቃም ሆኜ አቀርብለት ነበር።
38እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ እንደ ሆነ፥
ትልሞችዋም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደ ሆነ፥
39ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፥
የባለቤቶችንም ነፍስ አሳዝኜ እንደ ሆነ፥
40በስንዴ ፋንታ አሜከላ፥
በገብስም ፋንታ ኵርንችት ይውጣብኝ።
የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in