YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 51

51
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በባቢሎን ላይና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ አጥፊውን ነፋስ አስነሣለሁ። 2በባቢሎንም ላይ የሚያዘሩትን ሰዎች እሰድዳለሁ እነርሱም ያዘሩአታል፥ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፥ በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል። 3በወርዋሪው ላይ በጥሩርም በሚነሣው ላይ ቀስተኛው ቀስቱን ይገትር፥ ለጐበዛዝትዋ አትዘኑ ሠራዊትዋንም ሁሉ አጥፉ። 4በከለዳውያንም ምድር ተገድለው፥ በሜዳዋም ላይ ተወግተው ይወድቃሉ።
5ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል ምንም እንኳ የተሞላች ብትሆን፥ እስራኤልም ሆነ ይሁዳ በአምላኩ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ዘንድ አልተጣለም። 6ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ፥ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ፥ በበደልዋ አትጥፉ፥ የእግዚአብሔር በቀል ጊዜ ነውና፥ እርሱም ብድራትዋን ይከፍላታልና። 7ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ ነበረች፥ አሕዛብም ከጠጅዋ ጠጥተዋል፥ ስለዚህ አሕዛብ አብደዋል። 8ባቢሎን በድንገት ወድቃ ጠፍታለች፥ አልቅሱላት፥ ትፈወስም እንደ ሆነ ለቍስልዋ መድኃኒት ውሰዱላት። 9ባቢሎንን ፈወስናት፥ እርስዋ ግን አልተፈወሰችም፥ ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፥ እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ከፍ ብሎአልና ትታችኋት እያንዳንዳችን ወደ አገራችን እንሂድ። 10እግዚአብሔር ጽድቃችንን አውጥቶአል፥ ኑ፥ በጽዮን የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ሥራ እንናገር።
11ፍላጾችን ሳሉ ጋሻዎችንም አዘጋጁ፥ እግዚአብሔር ያጠፋት ዘንድ አሳቡ በባቢሎን ላይ ነውና የሜዶንን ነገሥታት መንፈስ አስነሥቶአል፥ የእግዚብሔር በቀል የመቅደሱ በቀል ነውና። 12በባቢሎን ቅጥር ዓላማውን አንሡበት፥ ጥበቃን አጽኑ፥ ተመልካቾችን አቁሙ፥ ድብቅ ጦር አዘጋጁ። እግዚአብሔር በባቢሎን በሚኖሩት ላይ የተናገረውን አስቦአልና፥ አድርጎአልምና። 13አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፥ በመዝገብም የበለጠግሽ ሆይ፥ እንደ ስስትሽ መጠን ፍጻሜሽ ደርሶአል። 14የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፦ በእውነት ሰዎችን እንደ አንበጣ እሞላብሻለሁ፥ እነርሱም ጩኸት ያነሡብሻል።
15ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 16ድምጹን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፥ ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 17ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፥ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። 18እነርሱም ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፥ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። 19የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፥ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፥ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
20አንቺ መዶሻዬና የጦር መሣሪያዬ ነሽ፥ በአንቺ አሕዛብን እሰባብራለሁ፥ በአንቺም መንግሥታትን አጠፋለሁ፥ 21በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፥ 22በአንቺም ሰረገላውንና በላዩ የሚቀመጠውን እሰባብራለሁ፥ በአንቺም ወንድንና ሴትን እሰባብራለሁ፥ በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እሰባብራለሁ፥ በአንቺም ጐልማሳውንና ቆንጆይቱን እሰባብራለሁ፥ 23በአንቺም እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፥ በአንቺም አራሹንና ጥማጁን እሰባብራለሁ፥ በአንቺም አለቆችንና ሹማምቶችን አሰባብራለሁ። 24በጽዮን በዓይናችሁ ፊት ስለሠሩት ክፋታቸው ሁሉ በባቢሎንና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ፍዳቸውን እከፍላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
25አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊ ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እጄንም እዘረጋብሃለሁ፥ ከድንጋዮችም ላይ አንከባልልሃለሁ፥ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ። 26ከአንተም ለማዕዘንና ለመሠረት የሚሆን ድንጋይ አይወስዱም፥ ለዘላለምም ባድማ ትሆናለህ፥ ይላል እግዚአብሔር።
27በምድር ላይ ዓላማን አንሡ በአሕዛብም መካከል መለከት ንፉ፥ አሕዛብንም አዘጋጁባት፥ የአራራትንና የሚኒን የአስከናዝንም መንግሥታት ሰብስቡባት አለቃንም በላይዋ አቁሙ፥ እንደ ጠጕራም ኩብኩባ ፈረሶችን በላይዋ አውጡ። 28አሕዛብን የሚዶንንም ነገሥታት አለቆችንም ሹማምቶችንም ሁሉ የግዛታቸውንም ምድር ሁሉ አዘጋጁባት። 29ማንም እንዳይቀመጥባት የባቢሎንን ምድር ባድማ ያደርጋት ዘንድ የእግዚአብሔር አሳብ በባቢሎን ላይ ጸንቶአልና ምድር ተናውጣለች ታመመችም። 30የባቢሎን ኃያላን መዋጋትን ትተዋል በአምባዎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፥ ኃይላቸውም ጠፍቶአል እንደ ሴቶችም ሆነዋል፥ ማደሪያዎችዋም ነድደዋል መወርወሪያዎችዋም ተሰብረዋል። 31-32ከዳር እስከ ዳር ድረስ ከተማው እንደ ተያዘች መልካዎችዋም እንደ ተያዙ፥ ቅጥርዋም በእሳት እንደ ተቃጠለ፥ ሰልፈኞችም እንደ ደነገጡ ለባቢሎን ንጉሥ ይነግር ዘንድ ወሬኛው ወሬኛውን መልእክተኛውም መልእክተኛውን ሊገናኝ ይሮጣል።
33የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ አውድማ እንደ ተረገጠ ጊዜ፥ እንዲሁ የባቢሎን ልጅ ናት፥ ጥቂት ቈይታ የመከር ጊዜ ይደርስባታል። 34የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላኝ፥ ከፋፈለኝም፥ እንደ ባዶ ዕቃም አደረገኝ፥ እንደ ዘንዶም ዋጠኝ፥ ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም ጣለኝ። 35በጽዮን የምትቀመጥ፦ በእኔና በሥጋዬ የተደረገ ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን ትላለች፥ ኢየሩሳሌምም፦ ደሜ በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን ትላለች። 36ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እምዋገትልሻለሁ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ፥ ባሕርዋንም ድርቅ አደርገዋለሁ ምንጭዋንም አደርቀዋለሁ። 37ባቢሎንም የድንጋይ ቍልልና የቀበሮ ማደሪያ መደነቂያም ማፍዋጫም ትሆናለች፥ የሚቀመጥባትም ሰው አይገኝም። 38በአንድነትም እንደ አንበሶች ያገሣሉ፥ እንደ አንበሳም ደቦሎች ያጕረመርማሉ። 39በሞቃቸው ጊዜ ደስ እንዲላቸው ለዘላለምም አንቀላፍተው እንዳይነቁ የመጠጥ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ አሰክራቸውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 40እንደ ጠቦቶችና እንደ አውራ በጎች እንደ አውራ ፍየሎችም ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።
41ሼሻክ እንዴት ተያዘች! የምድርም ሁሉ ምስጋና እንዴት ተወሰደች! ባቢሎንም በአሕዛብ መካከል መደነቂያ እንዴት ሆነች! 42ባሕር በባቢሎን ላይ ወጣ በሞገዱም ብዛት ተከደነች። 43ከተሞችዋ ባድማና ደረቅ ምድር ምድረ በዳም፥ ሰውም የማይቀመጥበት የሰውም ልጅ የማያልፍበት ምድር ሆኑ። 44በባቢሎንም ውስጥ ቤልን እቀጣለሁ የዋጠውንም ከአፉ አስተፋዋለሁ፥ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርሱ አይሰበሰቡም፥ የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል።
45ሕዝቤ ሆይ፥ ከመካከልዋ ውጡ እያንዳንዳችሁም ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ራሳችሁን አድኑ። 46በምድርም ከሚሰማ ወሬ የተነሣ አትፍሩ ልባችሁም የዛለ አይሁን፥ በአንድ ዓመት ወሬ ይመጣል፥ ከዚያም በኋላ በሌላው ዓመት ወሬ፥ በምድርም ላይ ግፍ ይመጣል፥ አለቃም በአለቃ ላይ ይነሣል። 47ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን የባቢሎን ምስሎች የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ምድርዋም ሁሉ ታፍራለች፥ ተወግተውም የሞቱት ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ። 48አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር በእነርሱም ያለው ሁሉ ስለ ባቢሎን እልል ይላሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 49ባቢሎንም ከእስራኤል ተወግተው የሞቱት እንዲወድቁ እንዳደረገች፥ እንዲሁ በባቢሎን ከምድሩ ሁሉ ተወግተው የሞቱት ይወድቃሉ።
50ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ፥ ሂዱ፥ አትቁሙ፥ እግዚአብሔርን ከሩቅ አስቡ፥ ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡ። 51ስድብን ስለ ሰማን አፍረናል፥ ባዕዳን ሰዎችም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገብተዋልና ነውር ፊታችንን ከድኖታል። 52ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን ምስሎችዋ የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር በምድርዋም ላይ ሁሉ የተወጉት ያንቋርራሉ። 53ባቢሎን ምንም ወደ ሰማይ ብትወጣ፥ የኃይልዋንም ከፍታ ብታጸና፥ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል፥ ይላል እግዚአብሔር።
54ከባቢሎን ጩኸት፥ ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰምቶአል። 55እግዚአብሔር ባቢሎንን አጥፍቶአታልና፥ ከእርስዋም ታላቁን ድምፅ ዝም አሰኝቶአልና፥ ሞገዳቸውም እንደ ብዙ ውኆች ይተምማል፥ የድምፃቸውም ጩኸት ተሰምቶአል። 56አጥፊው በባቢሎን ላይ መጥቶባታልና፥ ኃያላኖችዋ ተያዙ፥ ቀስታቸውም ተሰባበረ፥ እግዚአብሔር ፍዳን የሚከፍል አምላክ ነውና፥ ፍዳንም በእርግጥ ይከፍላል። 57መሳፍንቶችዋንና ጥበበኞችዋንም፥ አለቆችዋንና ሹማምቶችዋን ኃያላኖችዋንም አሰክራለሁ፥ ለዘላለምም አንቀላፍተው አይነቁም፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ። 58የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰፊው የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል ረጃጅሞችም በሮችዋ በእሳት ይቃጠላሉ፥ የወገኖችም ድካም ከንቱ ትሆናለች፥ የአሕዛብም ሥራ ለእሳት ትሆናለች፥ እነርሱም ይደክማሉ።
59የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ከእርሱ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘው ቃል ይህ ነው። ሠራያም የቤት አዛዥ ነበረ። 60በባቢሎንም ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ በመጽሐፍ ላይ ጻፈው። 61ኤርምያስም ሠራያን እንዲህ አለው፦ ወደ ባቢሎን በገባህ ጊዜ እይ፥ ይህንም ቃል ሁሉ አንብብና፦ 62አቤቱ፥ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት፥ ለዘላለምም ባድማ እንድትሆን ታጠፋት ዘንድ በዚህች ስፍራ ላይ ተናግረሃል በል። 63ይህንም መጽሐፍ ማንበብ ከፈጸምህ በኋላ፥ ድንጋይን እሰርበት በኤፍራጥስም ውስጥ ጣለው፥ 64አንተም፦ እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች አትነሣምም በል።
የኤርምያስ ቃል እስከዚህ ድረስ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in