ትንቢተ ኤርምያስ 50
50
1እግዚአብሔር ስለ ከለዳውያን ምድር ስለ ባቢሎን በነቢዩ በኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2በአሕዛብ መካከል ተናገሩ አውሩም፥ ዓላማውንም አንሡ፥ አውሩ፥ አትደብቁ፦ ባቢሎን ተወሰደች፥ ቤል አፈረ፥ ሜሮዳክ ደነገጠ፥ ምስሎችዋ አፈሩ፥ ጣዖታትዋ ደነገጡ በሉ። 3ሕዝብ ከሰሜን ወጥቶባታል ምድርዋንም ባድማ ያደርጋል፥ የሚቀመጥባትም አይገኝም፥ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል። 4በዚያም ወራት በዚያም ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ሆነው ይመጣሉ፥ እያለቀሱም መንገዳቸውን ይሄዳሉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ይፈልጋሉ። 5ፊታቸውንም ወደዚያ አቅንተው፦ ኑ፥ ከቶ በማይረሳ በዘላለም ቃል ኪዳን ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ ብለው ስለ ጽዮን መንገድ ይጠይቃሉ።
6ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፥ እረኞቻቸው አሳቱአቸው፥ በተራሮችም ላይ የተቅበዘበዙ አደረጉአቸው፥ ከተራራ ወደ ኮረብታ አለፉ፥ በረታቸውንም ረሱ። 7ያገኙአቸው ሁሉ በሉአቸው፥ ጠላቶቻቸውም፦ በጽድቅ ማደሪያ በእግዚአብሔር ላይ፥ በአባቶቻቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ስለ ሠሩ እኛ አልበደልንም አሉ። 8ከባቢሎን መካከል ሽሹ፥ ከከለዳውያንም ምድር ውጡ፥ በመንጎችም ፊት እንደ አውራ ፍየሎች ሁኑ። 9እነሆ፥ ከሰሜን ምድር የታላላቅ አሕዛብን ጉባኤ አስነሣለሁ በባቢሎንም ላይ አመጣቸዋለሁ፥ በእርስዋም ላይ ይሰለፋሉ፥ ከዚያም ትወሰዳለች፥ ፍላጾቻቸውም ባዶውን እንደማይመለስ እንደ ብልህ ጀግና ፍላጻ ናቸው። 10የከላውዴዎንም ምድር ትበዘበዛለች፥ የሚበዘብዙአትም ሁሉ ይጠግባሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
11ርስቴን የምትበዘብዙ እናንተ ሆይ፥ ደስ ብሎአችኋልና፥ ሐሤትንም አድርጋችኋልና፥ በመስክ ላይም እንዳለች ጊደር ሆናችሁ ተቀናጥታችኋልና፥ እንደ ብርቱዎችም ፈረሶች አሽካክታችኋልና፥ 12እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፥ የወለደቻችሁም ትጐሰቍላለች፥ እነሆ፥ በአሕዛብ መካከል ኋለኛይቱ ትሆናለች፥ ምድረ በዳና ደረቅ ምድር በረሀም ትሆናለች። 13ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ ሰው አይቀመጥባትም፥ በባቢሎንም በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይደነቃል በመጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጫል። 14እናንተ ቀስትን የምትገትሩ ሰዎች ሁሉ፥ በባቢሎን ላይ በዙሪያዋ ተሰለፉ፥ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርታለችና ወርውሩባት ፍላጾችንም አትንፈጉ። 15የእግዚአብሔር በቀል ነውና በዙሪያዋ ጩኹባት፥ እጅዋን ሰጠች፥ ግንቦችዋ ወደቁ ቅጥሮችዋም ፈረሱ፥ እርስዋን ተበቀሉ እንደ ሠራችውም ሥሩባት። 16ዘሪውንና በመከር ጊዜ ማጭድ የሚይዘውን ከባቢሎን አጥፉ፥ ከሚያስጨንቅ ሰይፍ ፊት እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።
17እስራኤል የባዘነ በግ ነው፥ አንበሶች አሳደዱት፥ መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፥ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አጥንቱን ቈረጠመው። 18ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ። 19እስራኤልንም ወደ ማሰማርያው እመልሳለሁ፥ በቀርሜሎስና በባሳንም ላይ ይሰማራል፥ ሰውነቱም በኤፍሬም ተራራና በገለዓድ ላይ ትጠግባለች። 20እነዚህን ያስቀረኋቸውን ይቅር እላቸዋለሁና በዚያን ወራት በዚያም ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የእስራኤል በደል የይሁዳም ኃጢአት ይፈለጋል ምንም አይገኝም።
21በምራታይም ምድር ላይ በፋቁድም በሚኖሩት ላይ ውጣ፥ ግደላቸው ፈጽመህም አጥፋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ አድርግ። 22የሰልፍና የታላቅ ጥፋት ውካታ በምድር ላይ አለ። 23የምድር ሁሉ መዶሻ እንዴት ደቀቀ እንዴትስ ተሰበረ! ባቢሎንስ በአሕዛብ መካከል እንዴት ባድማ ሆነች! 24ባቢሎን ሆይ፥ አጥምጄብሻለሁ አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፥ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ተዋጋሽ ተገኝተሻል ተይዘሽማል። 25የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በከለዳውያን ምድር ይሠራ ዘንድ ሥራ አለውና እግዚአብሔር ዕቃ ቤቱን ከፍቶ የቍጣውን ዕቃ ጦር አውጥቶአል። 26ከየበኩሉ በእርስዋ ላይ ውጡ፥ ጎተራዎችዋንም ክፈቱ፥ እንደ ክምርም አድርጓት ፈጽማችሁም አጥፉአት፥ አንዳችም አታስቀሩላት። 27ወይፈኖችዋን ሁሉ እረዱ፥ ወደ መታረድም ይውረዱ፥ ቀናቸው፥ የመጐብኘታቸው ጊዜ፥ ደርሶአልና ወዮላቸው! 28የአምላካችንን የእግዚአብሔርን በቀል የመቅደሱንም በቀል በጽዮን ይነግሩ ዘንድ ሸሽተው ከባቢሎን አገር ያመለጡት ሰዎች ድምፅ ተሰምቶአል።
29ቀስትን የሚገትሩትን ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩአቸው፥ በዙሪያዋ ስፈሩባት አንድም አያምልጥ፥ በእስራኤል ቅዱስ ላይ በእግዚአብሔር ላይ ኰርታለችና እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት፥ እንዳደረገችም ሁሉ አድርጉባት። 30ስለዚህ ጐበዛዝትዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፥ በዚያም ቀን ሰልፈኞችዋ ሁሉ ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 31ትዕቢተኛው ሆይ፥ የመጐብኘትህ ጊዜ፥ ቀንህ ደርሶአልና እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 32ትዕቢተኛው ተሰናክሎ ይወድቃል የሚያነሣውም የለም፥ በከተሞቹም ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፥ በዙሪያውም ያለውን ሁሉ ትበላለች።
33የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ተገፍተዋል፥ የማረኳቸውም ሁሉ በኃይል ይይዙአቸዋል፥ ይለቅቁአቸውም ዘንድ እንቢ ብለዋል። 34ተቤዢአቸው ብርቱ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፥ ምድርንም ያሳርፍ ዘንድ በባቢሎንም የሚኖሩትን ያውክ ዘንድ ሙግታቸውን ፈጽሞ ይምዋገታል። 35ሰይፍ በከለዳውያንና በባቢሎን በሚኖሩ ላይ፥ በአለቆችዋና በጥበበኞችዋ ላይ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር። 36ሰይፍ በሚጓደዱት ላይ አለ ሰነፎችም ይሆናሉ፥ ሰይፍም በኃያላኖችዋ ላይ አለ እነርሱም ይደነግጣሉ። 37ሰይፍ በፈረሶቻቸውና በሰረገሎቻቸው ላይ በመካከልዋም ባሉት በልዩ በልዩ ሕዝብ ሁሉ ላይ አለ፥ እነርሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ፥ ሰይፍም በመዝገብዋ ላይ አለ ለብዝበዛም ይሆናል። 38እርስዋ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናት፥ እነርሱም በጣዖታት ይመካሉና ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ። 39ስለዚህ የምድረ በዳ አራዊት ከተኩላዎች ጋር ይቀመጡባታል፥ ሰጐኖችም ይቀመጡባታል፥ ሰውም ከዚያ ወዲያ ለዘላለም አይቀመጥባትም፥ እስከ ልጅ ልጅም ድረስ የሚኖርባት የለም። 40ሰዶምንና ገሞራን በአጠገባቸውም የነበሩትን ከተሞች እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንዲሁ ሰው በዚያ አይቀመጥም የሰውም ልጅ አይኖርባትም።
41እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን ይመጣል ታላቅ ሕዝብና ብዙ ነገሥታትም ከምድር ዳርቻ ይነሣሉ። 42ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፥ ጨካኞች ናቸው ምሕረትም አያደርጉም፥ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፥ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፥ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ። 43የባቢሎን ንጉሥ ወሬአቸውን ሰምቶአል፥ እጁም ደክማለች፥ ጭንቀትም ይዞታል፥ ምጥ ወላድ ሴትን እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞታል። 44እነሆ፥ ከእርስዋ ዘንድ በቶሎ አባርራቸዋለሁና በጠነከረው አምባ ላይ ከዮርዳኖስ ትዕቢት ውስጥ እንደ አንበሳ ይወጣል፥ የተመረጠውንም በእርስዋ ላይ እሾመዋለሁ፥ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ ለእኔ ጊዜ የሚወስን ማን ነው? ወይስ ፊቴን የሚቃወም እረኛ ማን ነው? 45ስለዚህ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ የመከረባትን ምክር፥ በከለዳውያንም ምድር ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፥ በእውነት የመንጋ ትንንሾች ይጎተታሉ፥ በእውነት ማደሪያቸውን ባድማ ያደርግባቸዋል። 46ከባቢሎን መያዝ ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፥ ጩኸትም በአሕዛብ መካከል ዘንድ ተሰማ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 50: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in