YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 43

43
1የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ፥ ለእነርሱ አምላካቸው እግዚአብሔር የላከውን ይህን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ መናገርን በፈጸመ ጊዜ፥ 2የሆሻያ ልጅ ዓዛርያስ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ትዕቢተኞችም ሰዎች ሁሉ ኤርምያስን፦ ሐሰት ተናግረሃል፥ አምላካችን እግዚአብሔር፦ በዚያ ትቀመጡ ዘንድ ወደ ግብጽ አትግቡ ብሎ አልላከህም፥ 3ነገር ግን ከለዳውያን እንዲገድሉን ወደ ባቢሎንም እንዲማርኩን በእጃቸው አሳልፈህ ትሰጠን ዘንድ የኔርያ ልጅ ባሮክ በላያችን ላይ አነሣሥቶሃል አሉት። 4የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ በይሁዳ ምድር ይቀመጡ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም። 5የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ ከተሰደዱባቸው ከአሕዛብ ሁሉ የተመለሱትን የይሁዳን ቅሬታ ሁሉ፥ 6ወንዶችንና ሴቶችን ልጆችንም የንጉሡንም ሴቶች ልጆች፥ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከሳፋን ልጅ ከአኪቃም ልጅ ከጎዶልያስ ጋር የተዋቸውን ሰዎች ሁሉ፥ ነቢዩንም ኤርምያስን የኔርያንም ልጅ ባሮክን ወሰዱ፥ 7የእግዚአብሔርንም ቃል አልሰሙምና ወደ ግብጽ ምድር ገቡ፥ እስከ ጣፍናስ ድረስ መጡ።
8በጣፍናስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9ታላላቆችን ድንጋዮች በእጅህ ውሰድ፥ የይሁዳም ሰዎች እያዩ በጣፍናስ ባለው በፈርዖን ቤት ደጅ መግቢያ ሸሽጋቸው፥ 10እንዲህም በላቸው፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ልኬ ባሪያዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን አመጣለሁ፥ ዙፋኑንም እኔ በሸሸግኋቸው በእነዚህ ድንጋዮች ላይ አኖራለሁ፥ እርሱም ማለፊያውን ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል። 11መጥቶም የግብጽን ምድር ይመታል፥ ለሞትም የሚሆነውን ለሞት፥ ለምርኮም የሚሆነውን ለምርኮ፥ ለሰይፍም የሚሆነውን ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል። 12በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል ያቃጥላቸውማል ይማርካቸውማል፥ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፥ ከዚያም በሰላም ይወጣል። 13በግብጽም ምድር ያለውን የሄልዮቱን ከተማ ሐውልቶች ይሰብራል፥ የግብጽንም አማልክት ቤቶች በእሳት ያቃጥላል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in