YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 34

34
1የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ከእጁም ግዛት በታች ያሉ የምድር መንግሥታት ሁሉ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምንና ከተሞችዋን ሁሉ ይወጉ በነበረ ጊዜ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሂድ ለይሁዳም ንጉሥ ለሴዴቅያስ ተናገር እንዲህም በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ በእሳትም ያቃጥላታል፥ 3አንተም በእርግጥ ትያዛለህ በእጅም አልፈህ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም፥ ዓይንህም የባቢሎንን ንጉሥ ዓይን ታያለች፥ እርሱም ከአንተ ጋር አፍ ለአፍ ይናገራል፥ ወደ ባቢሎንም ትገባለህ። 4ነገር ግን፥ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፥ እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል፦ በሰይፍ አትሞትም፥ በሰላም ትሞታለህ እንጂ፥ 5ከአንተ በፊት እንደ ነበሩ እንደ ዱሮ ነገሥታት እንደ አባቶችህ መቃጠል፥ እንዲሁ ያቃጥሉሃልና፦ ወየው! ጌታ ሆይ እያሉ ያለቅሱልሃል፥ እኔ ቃልን ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
6-7የባቢሎንም ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳን ከተሞች ሁሉ፥ ከተመሸጉት ከይሁዳ ከተሞች የተረፉትን ለኪሶንና ዓዜቃን በወጋ ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ቃል ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው።
8-9ሰው ሁሉ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባሪያውንና ዕብራዊት የሆነች ሴት ባሪያውን አርነት እንዲያወጣ፥ አይሁዳዊ ወንድሙንም ማንም እንዳይገዛ፥ ስለ አርነታቸው አዋጅ እንዲነገር ንጉሡ ሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ከነበሩ ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 10ሰው ሁሉ ወንድ ባሪያውንና ሴት ባሪያውን አርነት እንዲያወጣ ከእንግዲህ ወዲህም ማንም እንዳይገዛቸው ወደ ቃል ኪዳኑ የገቡ አለቆች ሁሉና ሕዝቡ ሁሉ ሰሙ አርነትም አወጡአቸው። 11ነገር ግን ከዚያ በኋላ ተመልሰው አርነት ያወጡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቻቸውን አስመለሱ፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም አድርገው ገዙአቸው። 12ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁን ከባርነት ቤት ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከእነርሱ ጋር እንዲህ ብዬ ቃል ኪዳን አደረግሁ፦ 14ሰባት ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ የተሸጠላችሁን ስድስትም ዓመት የተገዛላችሁን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ አርነት ታወጡታላችሁ፥ እያንዳንዱም ያወጣዋል፥ አባቶቻችሁ ግን አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። 15እናንተም ዛሬ ተመልሳችሁ ሰው ሁሉ ባልንጀራውን አርነት ለማውጣት አዋጅ በመንገር ለዓይኔ ደስ የሚያሰኝን ነገር አድርጋችሁ ነበር፥ በስሜም በሚጠራበት ቤት ውስጥ በፊቴ ቃል ኪዳን አድርጋችሁ ነበር። 16ነገር ግን ተመልሳችሁ ስሜን አስነቀፋችሁ፥ እያንዳንዳችሁም በፈቃዳቸው እንዲሄዱ አርነት ያወጣችኋቸውን ወንድና ሴት ባሪያዎቻችሁን አስመለሳችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም እንዲሆኑላችሁ ገዛችኋቸው።
17ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰው ሁሉ ለወንድሙና ለባልንጀራው የአርነት አዋጅ ለመንገር እኔን አልሰማችሁም፥ እነሆ፥ እኔ ለሰይፍና ለቸነፈር ለራብም የአርነት አዋጅ እናገርባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በምድርም መንግሥታት ሁሉ መካከል እንድትበተኑ አደርጋችኋለሁ። 18ቃል ኪዳኔንም የተላለፉትን ሰዎች፥ እንቦሳውንም ቈርጠው በቍራጩ መካከል ባለፉ ጊዜ በፊቴ ያደረጉትን የቃል ኪዳንን ቃል ያልፈጸሙትን፥ 19የይሁዳን አለቆችና የኢየሩሳሌምን አለቆች ጃንደረቦችን ካህናትንም በእንቦሳም ቍራጭ መካከል ያለፉትን የአገሩን ሕዝብ ሁሉ፥ 20ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል። 21የይሁዳንም ንጉሥ ሴዴቅያስንና አለቆቹን ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ ከእናንተም ለተመለሱት ለባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ። 22እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ወደዚህችም ከተማ እመልሳቸዋለሁ፥ እርስዋንም ይወጋሉ ይይዙአትማል በእሳትም ያቃጥሉአታል፥ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የሌለበት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in