YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 33

33
1ኤርምያስ ገና በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል ሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል መጣለት፦ 2ስሙ እግዚአብሔር የሆነ፥ ያደረገው እግዚአብሔር፥ ያጸናውም ዘንድ የሠራው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 3ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ፥ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ። 4የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለአፈር ድልድልና ለምሽግ ስለ ፈረሱ ስለዚህች ከተማ ቤቶች፥ ስለ ይሁዳም ነገሥታት ቤቶች እንዲህ ይላልና፦ 5ከለዳውያን ለመዋጋት መጥተዋል፥ ነገር ግን በቍጣዬና በመዓቴ በገደልኋቸው ሰዎች ሬሳዎች ሊሞሉአቸው ነው፥ ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፊቴን ከዚህች ከተማ ሰውሬአለሁና። 6እነሆ፥ ፈውስንና መድኃኒትን አመጣላታለሁ፥ እፈውሳቸውማለሁ፥ የሰላምንና የእውነትን ብዛት እገልጥላቸዋለሁ። 7የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ቀድሞም እንደ ነበሩ አድርጌ እሠራቸዋለሁ። 8እኔንም ከበደሉበት ኃጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ እኔንም የበደሉኝን ያመፁብኝንም ኃጢአታቸውን ሁሉ ይቅር እላለሁ። 9ይህችም ከተማ እኔ የምሠራላቸውን በጎነት ሁሉ በሚሰሙ እኔም ስላመጣሁላቸው በጎነትና ሰላም ሁሉ በሚፈሩና በሚደነግጡ አሕዛብ ሁሉ ፊት ለደስታ ስም ለምስጋናም ለክብርም ትሆናለች።
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ፦ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት በምትሉአት በዚህች ስፍራ፥ የሚቀመጥባቸው በሌላ፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባድማ በሆኑ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ፥ 11የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ፦ እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ድምፅ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡት ድምፅ እንደ ገና ይሰማል። የምድርን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
12የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ባድማ ሆኖ፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባለው በዚህ ስፍራ በከተሞችም ሁሉ መንጎቻቸውን የሚያሳርፉት የእረኞች መኖሪያ ይሆናል። 13በደጋው ላይ ባሉ ከተሞች በቈላውም ባሉ ከተሞች በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ በብንያምም አገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች መንጎቹ በተቈጣጣሪው እጅ እንደ ገና ያልፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
14እነሆ፥ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 15በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፥ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። 16በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትቀመጣለች፥ የምትጠራበትም ስም፦ እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው። 17እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዳዊት ዘንድ አይታጣም፥ 18የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም።
19የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 20እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቀንና ሌሊት በወራቱ እንዳይሆን የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ 21በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከባሪያዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። 22የሰማይን ሠራዊት መቍጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባሪያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ።
23የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24ይህ ሕዝብ፦ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ እንዳይሆን ሕዝቤን አቃልለዋል። 25እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያላጸናሁ እንደሆነ፥ 26እኔም ደግሞ በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች ይሆኑ ዘንድ ከዘሩ እንዳልወስድ፥ የያዕቆብንና የባሪያዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፥ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸውማለሁና።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in