YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 8

8
1እግዚአብሔርም፦ ታላቅ ሰሌዳ ወስደህ፦ ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ በሰው ፊደል ጻፍበት። 2የታመኑትን ሰዎች ካህኑን ኦርዮንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ አለኝ። 3ወደ ነቢይቱም ቀረብሁ፥ እርስዋም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች። 4እግዚአብሔርም፦ ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና ስሙን፦ ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ ጥራው አለኝ። 5እግዚአብሔርም ደግሞ ተናገረኝ እንዲህም አለኝ፦ 6ይህ ሕዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውኃ ጠልቶአልና፥ ረአሶንንና የሮሜልዩንም ልጅ ወዶአልና 7ስለዚህ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ፥ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ፥ ያመጣባቸዋል፥ መስኖውንም ሁሉ ሞልቶ ይወጣል፥ በዳሩም ሁሉ ላይ ይፈስሳል፥ 8እየጎረፈም ወደ ይሁዳ ይገባል፥ እያጥለቀለቀም ያልፋል፥ እስከ አንገትም ይደርሳል፥ አማኑኤል ሆይ፥ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች። 9አሕዛብ ሆይ፥ ዕወቁና ደንግጡ፥ እናንተም ምድራችሁ የራቀ ሁሉ፥ አድምጡ፥ ታጠቁ፥ ደንግጡ፥ ታጠቁ፥ ደንግጡ። 10ተመካከሩ፥ ምክራችሁ ይፈታል፥ ቃሉን ተናገሩ፥ ቃሉም አይጸናም፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና። 11እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ እንዲህ ተናገረኝ፥ በዚህም ሕዝብ መንገድ እንዳልሄድ አስጠነቀቀኝ፥ እንዲህም አለኝ፦ 12ይህ ሕዝብ፦ ዱለት ነው በሚሉት ሁሉ፦ ዱለት ነው አትበሉ፥ መፈራታቸውንም አትፍሩ፥ አትደንግጡ። 13ነገር ግን የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፥ የሚያስፈራችሁና የሚያስደንግጣችሁም እርሱ ይሁን። 14እርሱም ለመቅደስ ይሆናል፥ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች ለእንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል። 15ብዙዎችም በእርሱ ይሰናከላሉ፥ ይወድቁማል፥ ይሰበሩማል፥ ይጠመዱማል፥ ይያዙማል። 16ምስክሩን እሰር፥ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ሕጉን አትም። 17ከያዕቆብም ቤት ፊቱን የመለሰውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፥ እተማመንበታለሁ። 18እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን። 19እነርሱም፦ የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ፥ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን? 20ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም። 21እነርሱም ተጨንቀውና ተርበው ያልፋሉ፥ በተራቡም ጊዜ ተቈጥተው ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይረግማሉ፥ ወደ ላይም ይመለከታሉ፥ 22ወደ ምድርም ይመለከታሉ፥ እነሆም፥ መከራና ጨለማ የሚያስጨንቅም ጭጋግ አለ፥ ወደ ድቅድቅም ጨለማ ይሰደዳሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in