YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 7

7
1እንዲህም ሆነ፥ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፥ ሊያሸንፉአትም አልቻሉም። 2ለዳዊትም ቤት፦ ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል የሚል ወሬ ተነገረ፥ የእርሱም ልብ የሕዝቡ ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ። 3እግዚአብሔርም ኢሳይያስን አለው፦ አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፥ 4እንዲህም በለው፦ ተጠበቅ፥ ዝምም በል፥ ስለ እነዚህ ስለሚጤሱ ስለ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፥ ስለ ሶርያና ስለ ረአሶን ስለ ሮሜልዩም ልጅ ቍጣ አትፍራ፥ ልብህም አይድከም። 5-6ሶርያና ኤፍሬም የሮሜልዩም ልጅ፦ ወደ ይሁዳ እንውጣ እናስጨንቀውም፥ እንስበረውም፥ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት ብለው ክፋት ስለ መከሩብህ፥ 7ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም። 8የሶርያ ራስ ደማስቆ ነው፥ የደማስቆም ራስ ረአሶን ነው፥ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራልና ሕዝብ አይሆንም፥ 9የኤፍሬምም ራስ ሰማርያ ነው፥ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። ባታምኑ አትጸኑም። 10እግዚእብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 11ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለምን። 12አካዝም፦ አልለምንም፥ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም አለ። 13እርሱም አለ፦ እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፥ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፥ 14ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፥ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። 15ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። 16ሕፃኑም ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች። 17እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፥ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው። 18በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ እግዚአብሔር በግብፅ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝምብ በአሦርም አገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል። 19ይመጡማል፥ እነርሱም ሁሉ በበረሐ ሸለቆ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በእሾህ ቍጥቋጦ ሁሉ ላይ በማሰማርያውም ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ። 20በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፥ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይበላል። 21በዚያን ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ሰው አንዲት ጊደርን ሁለት በጎችንም ያሳድጋል፥ 22ከሚሠጡት ወተት ብዛት የተነሣ ቅቤ ይበላል፥ በአገሪቱም መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል። 23በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ሺህ ብር የተገመተ ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ሥፍራ ሁሉ ለኵርንችትና ለእሾህ ይሆናል። 24ኵርንችትና እሾህ በምድር ሁሉ ላይ ነውና በፍላጻና በቀስት ወደዚያ ይገባሉ። 25በመቈፈርያም ወደ ተቈፈሩ ኮረብቶች ሁሉ ከኵርንችትና እሾህ ፍርሃት የተንሣ ወደዚያ አትሄድም፥ ነገር ግን የበሬ ማሰማርያና የበግ መራገጫ ይሆናል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in