ትንቢተ ሕዝቅኤል 4
4
1አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጡብን ወስደህ በፊትህ አኑራት የኢየሩሳሌምንም ከተማ ስዕል ሳልባት ክበባት፥ 2ምሽግም ሥራባት፥ አፈርም ደልድልባት፥ ሰፈርም አቁምባት፥ በዙሪያዋም የሚያፈርስ ግንድ አድርግባት። 3የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማይቱ መካከል ለብረት ቅጥር አድርገው፥ ፊትህንም ወደ እርስዋ አቅና፥ የተከበበችም ትሆናለች አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።
4አንተም በግራ ጐድንህ ተኛ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት አኑርባት በምትተኛበትም ቀን ቍጥር ኃጢአታቸውን ትሸከማለህ። 5እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀን ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፥ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ። 6እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ በቀኝ ጐድንህ ትተኛለህ፥ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፥ አንድን ዓመት አንድ ቀን አድርጌ አርባ ቀን ሰጥቼሃለሁ። 7ክንድህን ዕራቁቱን አድርገህ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ክቡ ታቀናለህ፥ ትንቢትም ትናገርባታለህ። 8እነሆም፥ ገመድ አደርግብሃለሁ፥ የምትከበብበትንም ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከጐድን ጐድንህ አትገላበጥም።
9አንተም ስንዴንና ገብስን ባቄላንና ምስርን ጤፍንና አጃን ወደ አንተ ውሰድ፥ በአንድ ዕቃም ውስጥ አድርገህ እንጀራ ጋግር፥ በጐድንህ እንደ ተኛህበት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ። 10የምትበላውም በሚዛን በየቀኑ ሀያ ሀያ ሰቅል ይሁን፥ በየጊዜው ትበላዋለህ። 11ውኃውንም በልክ የኢን መስፈሪያ ከስድስት እጅ አንድን እጅ ትጠጣለህ፥ በየጊዜው ትጠጣዋለህ። 12እንደ ገብስ እንጐቻም አድርገህ ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለሁ። 13እግዚአብሔርም፦ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች እነርሱን በምበትንባቸው በአሕዛብ መካከል ርኩስ እንጀራቸውን ይበላሉ አለው። 14እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ሰውነቴ አልረከሰችም፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጥንብና አውሬ የሰበረውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም አልሁ። 15እርሱም፦ እነሆ፥ በሰው ፋንድያ ፋንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ በእርሱም እንጀራህን ትጋግራለህ አለኝ። 16ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የኢየሩሳሌምን እንጀራ በትር እሰብራለሁ፥ እየፈሩም እንጀራን በሚዛን ይበላሉ፥ እየደነገጡም ውኃን በልክ ይጠጣሉ፥ 17ይህም እንጀራንና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲደነቁ፥ በኃጢአታቸውም እንዲሰለስሉ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 4: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in