ትንቢተ ሕዝቅኤል 2
2
1እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእግርህ ቁም እኔም እናገርሃለሁ አለኝ። 2በተናገረኝም ጊዜ መንፈስ ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገርኝንም ሰማሁ። 3እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁ ወደ ዓመፀኞች ሰዎች ወደ እስራኤል ልጆች እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፁብኝ። 4እነርሱ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፥ አንተም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው።
5እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ። 6አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ኵርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም፥ አትፍራቸው፥ ቃላቸውንም አትፍራ፥ አንተ ቃላቸውን አትፍራ፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። 7እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ።
8አንተ ግን፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ስማ እንደዚያ እንደ ዓመፀኛው ቤት ዓመፀኛ አትሁን፥ አፍህን ክፈት የምሰጥህንም ብላ። 9ባየሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፥ እነሆም፥ የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት። 10በፊቴም ዘረጋው፥ በውስጥና በውጭም ተጽፎበት ነበር፥ ልቅሶና ኃዘን ዋይታም ተጽፎበት ነበር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 2: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in