ትንቢተ ሕዝቅኤል 1
1
1በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ። 2ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት 3ከወሩም በአምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ ወደ ቡዝ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፥ 4እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ እንደሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ ነበረ። 5ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር። 6ለእያዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት። 7እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፥ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፥ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር። 8በክንፎቻቸውም በታች በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ፥ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው። 9ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ የተያያዘ ነበረ፥ ሲሄዱም አይገላምጡም ነበረ፥ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር። 10የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት ነበረ፥ ለአራቱም በስተ ቀኛቸው እንደ አንበሳ ፊት፥ በስተ ግራቸውም እንደ ላም ፊት ነበራቸው፥ ለአራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው። 11ክንፋቸውም በላይ ተዘርግቶ ነበር፥ የእያንዳንዱም ሁለት ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ ሁለት ሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር። 12እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፥ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር። 13በእንስሶቹ መካከል እንደሚነድድ የእሳት ፍም ያለ ምስያ ነበረ፥ በእንስሶች መካከል ወዲህና ወዲያ የሚሄድ እንደ ፋና ያለ ምስያ ነበረ፥ ለእሳቱም ፀዳል ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር። 14እንስሶቹም እንደ መብረቅ ምስያ ይሮጡና ይመለሱ ነበር።
15እንስሶችንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ እንስሶች አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ። 16የመንኰራኵሩም መልክ እንደ ቢረሌ ነበረ፥ አራቱም አንድ አምሳያ ነበሩ፥ ሥራቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ። 17በእያራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር። 18ቁመታቸውም የረዘመና የሚያስፈራ ነበረ፥ የአራቱም ክበብ ዙሪያው በዓይን ተሞልቶ ነበር። 19እንስሶቹም በሄዱ ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ሄዱ። እንስሶቹም ከምድር ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ መንኰራኵሮቹ ከፍ ከፍ አሉ። 20መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱ ሄዱ፥ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና መንኰራኵሮቹ በእነርሱ አጠገብ ከፍ ከፍ አሉ። 21የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና እነዚያ ሲሄዱ እነዚህ ይሄዱ ነበር፥ እነዚያም ሲቆሙ እነዚህ ይቆሙ ነበር፥ እነዚያም ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።
22ከእንስሶች ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር። 23ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት። 24ሲሄዱም የክንፎቻቸውን ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል የአምላክም ድምፅ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፥ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር። 25በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፥ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።
26በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፥ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። 27ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፥ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። 28በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 1: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in