YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ሕዝቅኤል 14

14
1ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። 2የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል። የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፥ እኔስ ከእነርሱ ልጠየቅን? 4-5ስለዚህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁሉም በጣዖቶቻቸው ከእኔ ተለይተዋልና የእስራኤልን ቤት በልባቸው እይዝ ዘንድ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ ብለህ ንገራቸው።
6ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ንስሐ ግቡ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ፊታችሁንም ከርኵሰታችሁ ሁሉ መልሱ። 7ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ፥ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ፥ 8ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ ከሕዝቤም መካከል አጠፋዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 9ነቢዩም ቢታለል ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እጄንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ ከሕዝቤም ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ። 10ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ እንደሚጠይቀውም ሰው ኃጢአት እንዲሁ የነቢዩ ኃጢአት ይሆናል። 11ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግሞ ከእኔ ርቀው እንዳይስቱ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው፥ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
12የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13የሰው ልጅ ሆይ፥ ምድር በማመፅ በእኔ ላይ ኃጢአት ስትሠራ፥ እኔም እጄን ስዘረጋባት የእንጀራዋንም በትር ስሰብር ራብን ስሰድድባት ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ሳጠፋ፥ 14እነዚህ ሦስት ሰዎች፥ ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም፥ ቢኖሩባት በጽድቃቸው የገዛ ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15ክፉዎቹን አራዊት በምድር ባሳልፍ እነርሱም ልጆችዋን ቢያጠፉ ስለ አራዊትም ማንም እንዳያልፍባት ባድማ ብትሆን፥ 16እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17ወይም በዚያች ምድር ላይ ሰይፍ አምጥቼ፦ ሰይፍ ሆይ፥ በምድሪቱ ላይ እለፊ ብል፥ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ባጠፋ፥ 18እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባት እኔ ሕያው ነኝና እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19ወይም በዚያች ምድር ላይ ቸነፈር ብሰድድ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ መዓቴን በደም ባፈስስባት፥ 20ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ይልቁንስ ሰውንና እንስሳን ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ ፍርዶቼን፥ ሰይፍንና ራብን ክፉዎችንም አውሬዎች ቸነፈርንም፥ ስሰድድባት! 22ነገር ግን፥ እነሆ፥ የሚያመልጡና ወንዶችና ሴቶች ልጆችን የሚያመጡ ይቀሩላታል፥ እነሆ፥ ወደ እናንተ ይወጣሉ እናንተም መንገዳቸውንና ሥራቸውን ታያላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ ስላመጣሁት ክፉ ነገር ሁሉ ስላመጣሁባትም ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ። 23መንገዳቸውንና ሥራቸውን ባያችሁ ጊዜ ያጽናኑአችኋል፥ ያደረግሁባትንም ሁሉ በከንቱ እንዳላደረግሁባት ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in