YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘጸአት 38

38
1ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን መሠዊያን ከግራር እንጨት አደረገ፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ከፍታው ሦስት ክንድ ነበረ። 2ቀንዶቹንም በአራቱ ማዕዘን አደረገበት፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ነበሩ፤ በናስም ለበጠው። 3የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አደረገ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አደረገ። 4እንደ መረብ ሆኖም የተሠራ የናስ መከታ ለመሠዊያ አደረገ፤ መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ ይደርስ ዘንድ በመሠዊያው በሚዞረው በደረጃው ታች አደረገው። 5ለናሱም መከታ ለአራቱ ማዕዘን የመሎጊያዎች ስፍራ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶች አደረገ። 6መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በናስም ለበጣቸው። 7ይሸከሙትም ዘንድ በመሠዊያ ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎቹን አገባ፤ ከሳንቆቹም ሠርቶ ባዶ አደረገው። 8የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ከሴቶች መስተዋት ከናስ አደረገ። 9አደባባዩንም አደረገ፤ በደቡብ ወገን ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ፥ የተፈተለ የጥሩ በፍታ መጋረጆች ነበሩ። 10ከናስ የተሠሩ ሀያውን ምሰሶችና ሀያውን እግሮች አደረገ፤ የምሰሶቹንም ኩላቦችና ዘንጎች ከብር አደረገ። 11በሰሜኑም ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ ከናስም የተሠራ ሀያ ምሰሶችንና ሀያ እግሮችን፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ። 12በምዕራብም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ አሥሩንም ምሰሶች፥ አሥሩንም የናስ እግሮች፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ። 13በምሥራቅም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች አደረገ። 14በአንድ ወገንም የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ፥ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ነበሩ። 15እንዲሁም በሁለተኛው ወገን በአደባባዩ ደጅ በዚህና በዚያ አሥራ አምስት ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ሦስትም ምሰሶች፥ ሦስትም እግሮች ነበሩ። 16በአደባባዩ ዙሪያ ያሉ መጋረጆች ሁሉ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ተሠርተው ነበር። 17የምሰሶቹም እግሮች የናስ፥ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ነበሩ፤ የምሰሶችም ጉልላቶች በብር ተለብጠው ነበር፤ በአደባባዩ ላሉ ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሩአቸው። 18የአደባባዩም ደጅ መጋረጃ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከጥሩም በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ ነበረ፤ ርዝመቱ ሀያ ክንድ ነበረ፥ ቁመቱም እንደ አደባባዩ መጋረጆች አምስት ክንድ ነበረ፤ 19ከናስ የተሠሩ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ነበሩ፤ ኩላቦቹ የብር ነበሩ፤ ጉልላቶቹና ዘንጎቹም በብር ተለብጠው ነበር። 20የማደሪያውም ካስማዎች በዙሪያውም ያለ የአደባባዩ ካስማዎች የናስ ነበሩ። 21በሙሴ ትእዛዝ ለሌዋውያን ማገልገል ሊሆን በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር እጅ እንደ ተቈጠረው የማደሪያው፥ የምስክሩ ማደሪያ፥ ዕቃ ድምር ይህ ነው። 22ከይሁዳ ነገድም የሆነ የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤል እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 23ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነ የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ነበረ፤ እርሱም የቅርጽ ሠራተኛና ብልህ ሠራተኛ፥ በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ፥ በጥሩም በፍታ የሚሠራ ጠላፊ ነበረ። 24የተሰጠው ወርቅ ሁሉ፥ በመቅደሱ ሥራ ሁሉ የተደረገው ወርቅ፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሀያ ዘጠኝ መክሊት ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ። 25በማኅበሩም ከሚቈጠሩት የተገኘ ብር፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ከሰባ አምስት ሰቅል ነበረ። 26እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የሰቅል ግማሽ ከተቈጠረው ከእያንዳንዱ ሰው የተሰጠ ነው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች ነበሩ። 27መቶውም የብር መክሊት የመቅደሱንና የመጋረጃውን እግሮች ለመሥራት ነበረ፤ ከመቶውም መክሊት መቶ እግሮች አደረገ፤ ለአንድ እግርም አንድ መክሊት ነበረ። 28ከሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅል የምሰሶቹን ኩላቦችና ዘንጎች አደረገ፥ የምሰሶቹንም ጉልላቶች ለበጠ። 29የተሰጠውም ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። 30ከእርሱም የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ እግሮች፥ የናሱንም መሠዊያ፥ ለእርሱም የሆነውን የናሱን መከታ፥ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ 31በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን እግሮች፥ የአደባባዩንም ደጃፍ እግሮች፥ የማደሪያውንም ካስማዎች ሁሉ በአደባባዩ ዙሪያም ያሉትን ካስማዎች ሁሉ አደረገ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in