ኦሪት ዘዳግም 34
34
1ሙሴም ከሞዓብ ሜዳ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ወደ ፈስጋ ራስ ወጣ፤ እግዚአብሔርም እስከዳን ድረስ ያለውን የገለዓድን ምድር፥ 2የንፍታሌምንም ምድር ሁሉ፥ የኤፍሬምንና የምናሴንም ምድር፥ እስከ ምዕራብም ባሕር ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር ሁሉ፥ ደቡቡንም፥ 3እስከ ዞዓር ድረስ ያለውንም የዘንባባ ዛፎች ያሉባትን ከተማ የኢያሪኮን ሸለቆ ሜዳ አሳየው። 4እግዚአብሔርም፦ ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማልሁላቸው ምድር ይህች ናት፤ በዓይንህ እንድታያት አደረግሁህ፥ ነገር ግን ወደዚያች አትሻገርም አለው። 5የእግዚአብሔር ባሪያም ሙሴ እንደ እግዚአብሔር ቃል በዚያ በሞዓብ ምድር ሞተ። 6በቤተ ፌጎርም ፊት ለፊት በሞዓብ ምድር በሸለቆው ውስጥ ተቀበረ፤ እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩን ማንም አላወቀም። 7ሙሴም በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ዓመት ነበረ፤ ዓይኑ አልፈዘዘም፥ ጉልበቱም አልደነገዘም። 8የእስራኤልም ልጆች በሞዓብ ሜዳ ሠላሳ ቀን ለሙሴ አለቀሱለት፤ ለሙሴም ያለቀሱለት የልቅሶው ወራት ተፈጸመ። 9ሙሴም እጆቹን ስለ ጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ፤ የእስራኤልም ልጆች ታዘዙለት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 10እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እንዳወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ ከዚያ ወዲህ በእስራኤል ዘንድ አልተነሣም፤ 11በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ምልክትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከው ያለ፥ 12በእስራኤል ሁሉ ፊት በጸናች እጅ ሁሉና በታላቅ ማስደንገጥ ሁሉ እንዳደረገው እንደ ሙሴ ያለ አልተነሣም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 34: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in