ኦሪት ዘዳግም 14
14
1-2እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድርም ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ እግዚአብሔር አንተን መርጦአልና ስለ ሞተው ሰው አካላችሁን አትንጩ፥ በዓይኖቻችሁም መካከል ራሳችሁን አትላጩ። 3-4ርኩስን ነገር ሁሉ አትብላ። የምትበሉአቸው እንስሶች እነዚህ ናቸው፤ 5በሬ፥ በግ፥ ፍየል፥ ዋላ፥ ሚዳቍ፥ የበረሃ ፍየል፥ አጋዘን፥ አጭ፥ በራይሌ፥ ድኩላ። 6ከእንስሶች ሰኮናው የተሰነጠቀውን፥ ጥፍሩም ከሁለት የተከፈለውን፥ የሚያመሰኳውንም እንስሳ ሁሉ ትበላለህ። 7ነገር ግን ከሚያመሰኩ ወይም ሰኮናቸው ከተሰነጠቀ እነዚህን አትበሉም፤ ግመልን፥ ጥንቸልን፥ ሽኮኮን አትበሉም። ያመሰኳሉና፥ ነገር ግን ሰኮናቸው አልተሰነጠቀምና እነዚህ ለእናንተ ርኩሶች ናቸው። 8እርያም ሰኮናው ስለ ተሰነጠቀ ነገር ግን ስላላመሰኳ፥ እርሱ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ ሥጋውን አትብሉ፥ በድኑንም አትንኩ። 9በውኆች ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው፤ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። 10ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸውን አትበሉም፤ ለእናንተ ርኩስ ናቸው። 11ንጹሕ የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ። 12ሊበሉ የማይገባቸው ግን እነዚህ ናቸው፤ 13ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭልፊት፥ ጭላት በየወገኑ፥ 14-15ቁራም ሁሉ በየወገኑ፥ ሰጎን፥ 16ጠላቍ፥ ዝዪ፥ በቍል በየወገኑ፥ ጉጉት፥ 17ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ 18እርኩም፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጅላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 19የሚበርርም ተንቀሳቃሽ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ አይበላም። 20ንጹሕ የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ። 21አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ነህና የበከተውን ሁሉ አትብላ፤ ይበላው ዘንድ በአገርህ ደጅ ለተቀመጠ መጻተኛ ትሰጠዋለህ፥ ወይም ለእንግዳ ትሸጠዋለህ። የፍየሉን ጠቦት በእናቱ ወተት አትቀቅል። 22ከእርሻህ በየዓመቱ ከምታገኘው ከዘርህ ፍሬ ሁሉ አሥራት ታወጣለህ። 23ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን የወይን ጠጅህንም የዘይትህንም አሥራት የላምህንና የበግህንም በኩራት ብላ። 24አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ፥ መንገዱ ሩቅ ቢሆን፥ አምላክህም እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው ስፍራ ቢርቅብህ፥ ይህን ወደዚያ ለመሸከም ባትችል፥ ትሸጠዋለህ፥ 25የዋጋውንም ገንዘብ በእጅህ ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትሄዳለህ። 26በዚያም በገንዘቡ ሰውነትህ የፈለገውን፥ በሬ ወይም በግ ወይም የወይን ጠጅ ወይም ብርቱ መጠጥ ሰውነትህም የሚሻውን ሁሉ ትገዛለህ፤ በዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፥ አንተና ቤተ ሰብህም ደስ ይላችኋል። 27ድርሻና ርስት ከአንተ ጋር ስለሌለው በአገርህ ደጅ ውስጥ ያለውን ሌዋዊ ቸል አትበል። 28በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ በዚያ ዓመት የፍሬህን አሥራት ሁሉ አምጥተህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ታኖረዋለህ፤ 29ሌዋዊውም፥ ከአንተ ጋር ክፍልና ርስት የለውምና፥ በአገርህም ደጅ ያለ መጻተኛ ድሀ አደግም መበለትም መጥተው ይበላሉ ይጠግባሉም፤ ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 14: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in