YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 26

26
1የዚፍ ሰዎችም ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል መጥተው፦ እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ ተሸሽጎአል አሉት። 2ሳኦልም ተነሥቶ ዳዊትን በዚፍ ምድረ በዳ ይሻ ዘንድ ከእስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎች ይዞ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ። 3ሳኦልም በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ በመንገዱ አጠገብ ሰፈረ። ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፥ ሳኦልም በስተ ኋላው ወደ ምድረ በዳ እንደ መጣ አየ። 4ዳዊትም ሰላዮች ሰደደ፥ ሳኦልም ወደዚህ እንደ መጣ በእርግጥ አወቀ። 5ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ መጣ፥ ሳኦልና የሠራዊቱ አለቃ የኔር ልጅ አበኔርም የተኙበትን ስፍራ አየ፥ ሳኦልም በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር፥ ሕዝቡም በዙሪያው ሰፍሮ ነበር።
6ዳዊትም ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የጽሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን፦ ወደ ሳኦል ወደ ሰፈሩ ከእኔ ጋር የሚወርድ ማን ነው? ብሎ ጠየቃቸው፥ አቢሳም፦ እኔ ከአንተ ጋር እወርዳለሁ አለ። 7ዳዊትና አቢሳም ወደ ሕዝቡ በሌሊት መጡ፥ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩ በራሱ አጠገብ በምድር ተተክሎ በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር። አበኔርና ሕዝቡም በዙሪያው ተኝተው ነበር። 8አቢሳም ዳዊትን፦ ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶታል፥ አሁንም እኔ በጦር አንድ ጊዜ ከምድር ጋር ላጣብቀው፥ ሁለተኛም አያዳግምም አለው። 9ዳዊትም አቢሳን፦ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንምና አትግደለው አለው። 10ደግሞም ዳዊት፦ ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ይመታዋል፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፥ ወይም ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል፥ 11እኔ ግን እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው፥ አሁንም በራሱ አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃውን መንቀል ይዘህ እንሂድ አለ። 12ዳዊትም በሳኦል ራስ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውኃውን መንቀል ወሰደ፥ ማንም ሳያይ ሳያውቅም ሄዱ፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ወድቆባቸው ነበርና ሁሉ ተኝተው ነበር እንጂ የነቃ አልነበረም።
13ዳዊትም ወደዚያ ተሻገረ፥ በተራራውም ራስ ላይ ርቆ ቆመ፥ በመካከላቸውም ሰፊ ስፍራ ነበረ። 14ዳዊትም ለሕዝቡና ለኔር ልጅ ለአበኔር፦ አበኔር ሆይ፥ አትመልስምን? ብሎ ጮኸ። አበኔርም መልሶ፦ ለንጉሡ የምትጮኸው አንተ ማን ነህ? አለ። 15ዳዊትም አበኔርን፦ አንተ ጕልማሳ አይደለህምን? በእስራኤል ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? ጌታህን ንጉሡን ለመግደል አንድ ሰው ገብቶ ነበርና ጌታህን ንጉሡን የማትጠብቅ ስለ ምን ነው? 16ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እናንተ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና ሞት ይገባችኋል፥ አሁንም የንጉሡ ጦርና በራሱ አጠገብ የነበረው የውኃው መንቀል የት እንደ ሆነ ተመልከት አለው። 17ሳኦልም የዳዊት ድምፅ እንደ ሆነ አውቆ፦ ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለው። ዳዊትም፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ድምፄ ነው አለው። 18ደግሞ አለ፦ ጌታዬ ባሪያውን ስለ ምን ያሳድዳል? ምን አደረግሁ? ምንስ ክፋት በእጄ ላይ ተገኘብኝ? 19አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የእኔን የባሪያህን ቃል ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፥ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አስነሥቶህ እንደ ሆነ፥ ቁርባንን ይቀበል፥ የሰው ልጆች ግን ቢሆኑ፦ ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ላይ እንዳልቀመጥ ዛሬ ጥለውኛልና በእግዚአብሔር ፊት ርጉማን ይሁኑ። 20አሁንም በተራራው ላይ ሰው ቆቅን እንደሚሻ የእስራኤል ንጉሥ ነፍሴን ለመሻት ወጥቶአልና ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ አይፍሰስ።
21ሳኦልም፦ በድያለሁ፥ ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ተመለስ፥ ዛሬ ነፍሴ በዓይንህ ፊት ከብራለችና ከዚህ በኋላ ክፉ አላደርግብህም፥ እነሆ፥ ስንፍና አድርጌአለሁ፥ እጅግ ብዙም ስቻለሁ አለ። 22ዳዊትም መልሶ አለ፦ የንጉሥ ጦር እነሆ፥ ከብላቴኖችም አንድ ይምጣና ይውሰዳት። 23ዛሬም እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶህ ሳለ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ አልወደድሁምና ለሁሉ እያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ጽድቁና እንደ እምነቱ ፍዳውን ይክፈለው። 24ነፍስህም ዛሬ በዓይኔ ፊት እንደ ከበረች እንዲሁ ነፍሴ በእግዚአብሔር ዓይን ፊት ትክበር፥ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ። 25ሳኦል ዳዊትን፦ ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ቡሩክ ሁን፥ ማድረግን ታደርጋለህ፥ መቻልንም ትችላለህ አለው። ዳዊትም መንገዱን ሄደ፥ ሳኦልም ወደ ሰፍራው ተመለሰ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in