መዝሙረ ዳዊት 34
34
የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ፥ የሚበድሉኝን በድላቸው፥
የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው።
2ጋሻና ጦር ያዝ፥
እኔንም ለመርዳት ተነሥ።
3ሰይፍህን ምዘዝ፥ የሚከብቡኝንም ክበባቸው#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሚያሳድዱኝን ክበባቸው” ይላል።
ነፍሴን፦ ረዳትሽ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “መድኀኒትሽ” ይላል። እኔ ነኝ በላት።
4ነፍሴን የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐሳቈሉም፤
ክፋትን በእኔ ላይ የሚመክሩ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሚያስቡ” ይላል። ይፈሩ፥ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ።
5በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥
የእግዚአብሔርም መልአክ ያስጨንቃቸው።
6መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ትሁን፥
የእግዚአብሔርም መልአክ ያሳድዳቸው።
7በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥
ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋታልና።
8ያላወቋት ወጥመድ ትምጣባቸው፥
የሸሸጓትም ወጥመድ ትያዛቸው፤
በዚህችም ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ።
9ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፥
በማዳኑም ሐሤት ታደርጋለች።
10አጥንቶች ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦
“አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው?
ድሃውን ከሚቀማው እጅ
ድሃውንና ችግረኛውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ።”
11የዐመፃ ምስክሮች ተነሡብኝ፥
የማላውቀንም በእኔ ላይ ተናገሩ።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “የማላውቀውን ጠየቁኝ” ይላል።
12ስለ በጎ ፋንታ ክፉን መለሱልኝ፥
ሰውነቴንም ልጆችን አሳጡአት።
13እኔስ ባሠቃዩኝ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥
ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤
ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ።
14ለወዳጆቼና ለወንድሞቼ እንደማደርግ አደረግሁ፤
እንደሚያለቅስና እንደሚተክዝ
ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ።
15በእኔ ላይ ተሰበሰቡ፥ ደስም አላቸው፤
ይገርፉኝ ዘንድ ተማከሩ፥ እኔ ግን አላወቅሁም።
ተሰበሩ፥ አልደነገጡምም።
16ፈተኑኝ፥ በእኔ ላይም ዘበቱብኝ፥ ሣቁብኝም፤#“ሣቁብኝ” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቀጩ።
17አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ትፈርድልኛለህ?
ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፥
ብቸኝነቴንም ከአንበሶች አድናት፥
18አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “አመሰግናለሁ” ይላል።
በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ።
19በግፍ የሚጠሉኝ በላዬ ደስ አይበላቸው፥
በከንቱ የሚጠሉኝና በዐይናቸው የሚጠቃቀሱብኝም።#ዕብ. “አይጠቃቀሱብኝ” ይላል።
20ለእኔስ ሰላምን ይናገሩኛልና፥
በግርፋትም ያጠፉኝ ዘንድ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “በቍጣም ሺንገላን ይመክራሉ” ይላል። ይመክራሉ።
21አፋቸውንም በእኔ ላይ አላቀቁ፤
እሰይ፥ እሰይ፥ በዐይናችን አየነው ይላሉ።
22አቤቱ፥ አንተ እይ፥ ዝምም አትበል፤
አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ።
23አቤቱ ተነሥ፥ ፍርዴንም አድምጥ፥
አምላኬ ጌታዬም፥ በክርክሬ ጊዜ ተነሥ፥
24አቤቱ፥ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፥
በእኔም ላይ ደስ አይበላቸው።
25በልባቸውም በሰውነቴ ላይ፥ “እሰይ እሰይ፥” አይበሉ፤
“ዋጥነውም” አይበሉ።
26በመከራዬ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፥ ይጐስቍሉም፤
በእኔ ላይ ነገርን የሚያበዙ እፍረትንና ጕስቍልናን ይልበሱ።
27ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው፥
ሐሤትንም ያድርጉ፤
የባሪያህን ሰላም የሚወዱ
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ታላቅ ነው ይበሉ።
28ምላሴ ጽድቅህን፥
ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 34: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in