ኦሪት ዘኍልቍ 21
21
በከነዓናውያን ላይ የተገኘ ድል
1በአዜብ በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የአራድ ንጉሥ በአታሪን መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ። 2እስራኤልም ለእግዚአብሔር፥ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ብትሰጠን እርሱንና ከተሞቹን ሕርም ብለን እናጠፋዋለን” ብለው ስእለት ተሳሉ። 3እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፤ ከነዓናውያንንም አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ እነርሱንም፥ ከተሞቻቸውንም ሕርም ብለው አጠፉአቸው፤ የዚያን ስፍራ ስም “ሕርም” ብለው ጠሩት።
መርዘኛው እባብና ከነሐስ የተሠራው እባብ
4ከሖርም ተራራ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የኤዶምንም ምድር ዞሩአት፤ ሕዝቡም በመንገድ ተበሳጩ። 5ሕዝቡም፥ “በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣኸን?” ብለው እግዚአብሔርንና ሙሴንም አሙ። “እንጀራ የለም፤ ውኃም የለምና፥ ሰውነታችንም ይህን ጥቅም የሌለው እንጀራ ተጸየፈች” ብለው ተናገሩ። 6እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ የሚገድሉ እባቦችን ሰደደ፤ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙ ሰዎች ሞቱ። 7ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው፥ “በእግዚአብሔርና በአንተ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አሉት። ሙሴም ስለ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 8እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “የናስ እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ እባቡም ሰውን ቢነድፍ የተነደፈው ሁሉ ይመልከተው፤ ይድናልም” አለው። 9ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።
ወደ ሞዐብ ሸለቆ የተደረገ ጕዞ
10የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፤ በኦቦትም ሰፈሩ። 11ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል በጌልጋይ#ዕብ. “በዒዬዓባሪም” ይላል። ሰፈሩ። 12ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። 13ከዚያም ተጕዘው ከአሞራውያን ዳርቻ በሚወጣው ምድረ በዳ ውስጥ በአርኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና። 14ስለዚህ በመጽሐፍ ተባለ የእግዚአብሔር ጦርነት ዞኦብንና የአርኖን ሸለቆዎችን አቃጠለ። 15ወደ ዒር ማደሪያ የሚወርድ፥ በሞዓብ ዳርቻም የሚጠጋ የሸለቆዎች ፈሳሾችንም አቆመ። 16ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፥ “ሕዝቡን ሰብስብ፤ የሚጠጡት ውኃ እሰጣቸዋለሁ” ብሎ ወደ ተናገረላት ጕድጓድ ሄዱ። 17በዚያም ጊዜ እስራኤል በዚያ ጕድጓድ አጠገብ ይህን መዝሙር ስለ ጕድጓዱ መዘመር ጀመሩ፦
18“አለቆች ቈፈሩአት፥
በበትረ መንግሥት፥ በበትራቸውም፥
የአሕዛብ ነገሥታት በመንግሥታቸውና በግዛታቸው አጐደጐዱአት።”#ዕብ. ምዕ. 21 ቍ. 17 እና 18 “አንተ ምንጭ ሆይ ፍለቅለት ፤ በበትረ መንግሥት፥ በበትራቸው የሕዝብ አዛውንት ያጐደጐዱአት፥ አለቆችም የቈፈሩአት ጕድጓድ” ይላል።
19ከዚያችም ምንጭ ወደ መንተናይን ተጓዙ፤ ከመንተናይንም ወደ ነሃልያል፥ ከነሃልያልም ወደ ባሞት፥ 20ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሃ ወዳለው ወደ ያኒን ሸለቆ ተጓዙ።
በንጉሥ ሴዎንና በንጉሥ አግ ላይ የተገኘ ድል
(ዘዳ. 2፥26፤ 3፥11)
21እስራኤልም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሙሴ” ይላል። ወደ አሞሬዎናውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን በሰላም ቃል እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ላከ፤ 22“በምድርህ ላይ እንለፍ፤ በመንገዱም እንሄዳለን፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጕድጓድህም ውኃን አንጠጣም፤ እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጎዳና እንሄዳለን።” 23ሴዎንም እስራኤል በወሰኑ ላይ ያልፉ ዘንድ አልፈቀደም፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፤ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፤ ወደ ኢያሶንም መጣ፤ እስራኤልንም ተዋጋቸው። 24እስራኤልም በሰይፍ መታው፤ ምድሩንም ከአርኖን ጀምሮ እስከ አሞን ልጆች እስከ ያቦቅ ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ ኢያዜር ነበረ። 25እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ። 26ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ ከአሮኤር እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ወስዶ ነበር።
27ስለዚህ የምሳሌ ሰዎች እንዲህ ብለው ይናገራሉ፦
“ወደ ሐሴቦን ኑ፤
የሴዎን ከተማ ይመሥረት፤ ይገንባ፤
28እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤
እስከ ሞዓብ ድረስ በላ፤ የአርኖን ሐውልቶችንም ዋጠ፤#ዕብ. “የሞዓብን ዔር የዓርኖንን ተራራ አለቆች በላ” ይላል።
29ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ!
የካሞስ ሕዝብ ሆይ፥ ጠፋህ፤
ወንዶች ልጆቻቸውን ለማደን፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለምርኮ፤
ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ።
30ዘራቸውም#ዕብ. “ገተርናቸው” ይላል። ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፋ፤
ሴቶቻቸውም ደግሞ በሞዓብ ላይ እሳትን አነደዱ።”#ዕብ. “ኖፋም እስኪደርሱ እስከ ሜድባ አፈረስናቸው” ይላል።
31እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ተቀመጡ። 32ሙሴም ሰላዮቹን ወደ ኢያዜር ላከ፤ እርስዋንና መንደሮችዋንም ያዙ፤ በዚያም የነበሩትን አሞሬዎናውያንን አባረሩ።
33ተመልሰውም በባሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይን ይወጋቸው ዘንድ ወጣ። 34እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ፥ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼሃለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞሬዎን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲሁ ታደርግበታለህ” አለው። 35እርሱንና ልጆቹን፥ ሕዝቡን ሁሉ አንድ ሰው ሳያመልጥ መቱ፤ ምድሩንም ወረሱ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 21: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in