YouVersion Logo
Search Icon

የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 12

12
ስለ ወይን አትክልቱ ሠራተኞች ምሳሌ
(ማቴ. 21፥33-46ሉቃ. 20፥9-19)
1በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። “አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 2በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ 3ይዘውም ደበደቡት፤ ባዶውንም ሰደዱት። 4ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ፤ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት፤ አዋርደውም ሰደዱት። 5ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፤ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ፤ አንዳንዱንም ገደሉ። 6የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ‘ልጄንስ ያፍሩታል፤’ ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ። 7እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለው፤ ርስቱም ለኛ ይሆናል፤’ ተባባሉ። 8ይዘውም ገደሉት፤ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት። 9እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ያጠፋል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።
10-11‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን
ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤
ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው።’
የሚለውን ይህን መጽሐፍ አላነበባችሁምን?”
12ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ።
ለቄሳር ግብር ስለ መክፈል
(ማቴ. 22፥15-22ሉቃ. 20፥20-26)
13በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ። 14መጥተውም “መምህር ሆይ! የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሳር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ?” አሉት። 15እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ፤” አላቸው። 16እነርሱም አመጡለት። “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” አላቸው፤ እነርሱም “የቄሳር ናት፤” አሉት። 17ኢየሱስም መልሶ “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። በእርሱም ተደነቁ።
ስለ ትንሣኤ ሙታን
(ማቴ. 22፥23-33ሉቃ. 20፥27-40)
18ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም አሉት 19“መምህር ሆይ! ሙሴ “የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ፤’ ብሎ ጻፈልን። 20ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤ 21ሁለተኛውም አገባት፤ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 22ሰባቱም አገቡአት፤ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። 23ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?”
24ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? 25ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። 26ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር
‘እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም
አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤’
እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? 27የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።”
ከሁሉ የምትበልጥ ትእዛዝ
(ማቴ. 22፥34-40ሉቃ. 10፥25-28)
28ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ “ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት?” ብሎ ጠየቀው። 29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ 30አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኀይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ፤’ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። 31ሁለተኛይቱም ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤’ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።” 32ጻፊውም “መልካም ነው፤ መምህር ሆይ! ‘አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ የለም፤’ ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ 33በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኀይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው፡” አለው። 34ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰ አይቶ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም፤” አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።
ኢየሱስ ለፈሪሳውያን ያቀረበው ጥያቄ
(ማቴ. 22፥41-46ሉቃ. 20፥41-44)
35ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ “ጻፎች ‘ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው፤’ እንዴት ይላሉ? 36ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ
‘ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ
እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ።’
37ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር።
ከጻፎች ሥራ ስለ መጠበቅ
(ማቴ. 23፥1-36ሉቃ. 20፥45-47)
38-39ሲያስተምርም እንዲህ አለ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብዣም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ 40የመበለቶችን ቤት የሚበሉ፤ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።”
የመበለቲቱ ስጦታ
(ሉቃ. 21፥1-4)
41ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ 42አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። 43ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ “እውነት እላችኋለሁ፤ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ 44ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች፤” አላቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in