ኦሪት ዘሌዋውያን 7
7
ስለ በደል መሥዋዕት ሕግ
1“የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 2የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደሉን መሥዋዕት በግ በዚያ ያርዱታል፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 3ስቡንም ሁሉ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ፥ በአንጀቱም ላይ ያለውን ስብ፤ 4ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ካህኑ ይለያል። 5ካህኑም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል፤ እርሱም የበደል መሥዋዕት ነው። 6ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 7የኀጢአት መሥዋዕት እንደ ሆነ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ለሁለቱ አንድ ሕግ ነው፤ በእነርሱ የሚያስተሰርይ ካህን ይወስደዋል። 8የሰውን የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን ያቀረበው የሚቃጠለው መሥዋዕት ቍርበት ለዚያው ካህን ይሆናል። 9በእቶን የተጋገረው የእህል ቍርባን ሁሉ፥ በመቀቀያም ወይም በምጣድ የበሰለው ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል።#ምዕ. 7 ቍ. 9 በግእዙ የለም። 10በዘይትም የተለወሰው ወይም የደረቀው የእህል ቍርባን ሁሉ ለአሮን ልጆች ሁሉ ይሆናል፤ ለእያንዳንዱም እኩል ይሆናል።
ስለ ደኅንነት መሥዋዕት ሕግ
11“ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 12ለምስጋና ቢያቀርበው፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም የስንዴ ዱቄት ያቀርባል። 13ለምስጋና የሚሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት በአቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል። 14ከቍርባኑም ሁሉ የእግዚአብሔርን ድርሻ ከእነርሱ አንዱን ያነሣል። እርሱም የደኅንነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል።
15“ለምስጋና የሚሆነው የደኅንነት መሥዋዕት ሥጋም ለእርሱ ነው፤ በሚቀርብበትም ቀን ይበሉታል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያተርፉም። 16የቍርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱ በሚቀርብበት ቀን ይብሉት፤ ከእርሱም የቀረውን በነጋው ይብሉት፤ 17ከመሥዋዕቱም ሥጋ እስከ ሦስተኛው ቀን የሚቈየውን በእሳት ያቃጥሉታል። 18በሦስተኛው ቀን ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርም፤ ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቍርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ከእርሱም የበላ ሰው ኀጢአቱን ይሸከማል።
19“ርኩስ ነገር የሚነካውን ሥጋ አይብሉት፤ በእሳት ያቃጥሉት እንጂ። ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ግን ከሥጋው ይብላ። 20ኀጢአት ሳለባት፥ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ የበላች ሰውነት፥ ያች ሰውነት ከሕዝብዋ ተለይታ ትጥፋ። 21ከርኩስ ሁሉ፥ ወይም ከረከሰው ሰው፥ ወይም ንጹሕ ካልሆነው እንስሳ የነካች ሰውነት፥ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ብትበላ፥ ያች ሰውነት ከሕዝብዋ ተለይታ ትጥፋ።”
ስብንና ደምን መብላት ስለማይገባ
22እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 23“የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ። 24የሞተውን ስብ፥ አውሬ የሰበረውንም ስብ ለሌላ ተግባር አድርጉት፤ እናንተ ግን አትብሉት፤ 25ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሁሉ ያች የበላች ሰውነት ከሕዝብዋ ተለይታ ትጥፋ። 26በመኖሪያዎቻችሁ ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን አትብሉ። 27ደም የምትበላ ሰውነት ሁሉ ያች ሰውነት ከሕዝብዋ ተለይታ ትጥፋ።”
ከደኅንነቱና ከሚቃጠለው መሥዋዕት የካህናት ዕድል ፈንታ
28እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 29“የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ ለእግዚአብሔር የደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቍርባኑን ለእግዚአብሔር ከደኅንነቱ መሥዋዕት ያመጣል። 30የእርሱ እጆች ለእግዚአብሔር የእሳቱን ቍርባን ያመጣሉ፤ ፍርምባውን በእግዚአብሔር ፊት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ በጉበቱ ላይ ያለውን መረብና የፍርምባውን ስብ ያመጣል። 31ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ይጨምረው፤ ፍርምባውም ለአሮንና ለልጆቹ ይሁን። 32ከደኅንነት መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን ለማንሣት ቍርባን እንዲሆን ለካህኑ ትሰጡታላቸሁ። 33ከአሮንም ልጆች የደኅንነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርብ ለእርሱ ቀኝ ወርቹ እድል ፈንታው ይሆናል። 34ፍርምባውንና የቀኝ ወርቹን ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕታቸው ወስጄአለሁ፤ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘለዓለም ሕግ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ሰጥቼአቸዋለሁ።”
35እግዚአብሔርን በክህነት ያገለግሉት ዘንድ በተቀቡበት ቀን ለእግዚአብሔር ከሆነ ከእሳት ቍርባን የአሮንና የልጆቹ ሕግ ይህ ነው። 36ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም ሕግ እንዲሆን በቀባቸው ቀን የእስራኤል ልጆች ይሰጡአቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው። 37የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን፥ የኀጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 38እግዚአብሔር በሲና ምድረ በዳ ቍርባናቸውን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርቡ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 7: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in