ኦሪት ዘሌዋውያን 4
4
የኀጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ሳያውቅ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ 3የተቀባውም ሊቀ ካህናት በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኀጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኀጢአቱ ከመንጋው ነውር የሌለበትን ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኀጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል። 4ወይፈኑንም ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፤ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል። 5ተቀብቶ የተሾመው ካህን ከወይፈኑ ደም በእጁ ወስዶ ወደ ምስክሩ ድንኳን ያመጣዋል፤ 6ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 7ካህኑም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የወይፈኑንም ደም ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 8ለኀጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 9ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥ 10ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል፤ ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቀርበዋል። 11የወይፈኑን ቍርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ ፈርሱንም፤ 12ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስዱታል፤ በዕንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥሉታል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል።
13“የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከማኅበሩ ዐይን ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፤ 14ከዚህም በኋላ፥ የሠሩት ኀጢአት ቢታወቃቸውና ንስሓ ቢገቡ ማኅበሩ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ ምስክሩም ድንኳን ፊት ያመጡታል። 15የማኅበሩም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርዱታል። 16የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ ምስክሩ ድንኳን ያመጣል፤ 17ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 18በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 19ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል። 20እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንደ አደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ኀጢአታቸውን ያስተሰርያል፤ ኀጢአቸውም ይሰረይላቸዋል። 21ወይፈኑንም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስዱታል፤ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠሉ ያቃጥሉታል፤ የማኅበሩ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና።
22“መኰንንም ኀጢአትን ቢሠራ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ እንዲህም ቢበድል፥ 23የሠራው ኀጢአት ቢታወቀውና ንስሓ ቢገባ፥ ከፍየሎች ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርባል፤ 24በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። 25ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 26ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ፥ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ካህኑም ኀጢአቱን ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል።
27“ከሀገሩም ሕዝብ አንድ ሰው ኀጢአትን ሳያውቅ ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ ቢበድልም፥ 28ለእርሱም የሠራው ኀጢአት ቢታወቀውና ንስሓ ቢገባ፥#“ንስሓ ቢገባ” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ስለ ሠራው ኀጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቍርባኑ ያመጣል። 29እጁንም በኀጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት እንስሳትን በሚያርዱበት ስፍራ የኀጢአት መሥዋዕት ፍየልዋን ያርዳታል። 30ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። 31ስቡም ሁሉ ከደኅንነት መሥዋዕት ላይ እንደሚወሰድ፥ ስብዋን ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል።
32“ስለ ኀጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። 33እጁንም በኀጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኀጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። 34ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። 35ስቡ ሁሉ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው የበግ ጠቦት ላይ እንደሚወሰድ ስብዋን ሁሉ ይወስዳሉ፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 4: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in