ትንቢተ ዮናስ 4
4
የእግዚአብሔር ምሕረትና የዮናስ ብስጭት
1ዮናስም ፈጽሞ አዘነ፤ ተከዘም። 2ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ በሀገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የምትመለስ አምላክ እንደ ሆንህ ዐውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር። 3አሁንም አቤቱ! ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ! ነፍሴን ከእኔ ውሰድ።” 4እግዚአብሔርም ዮናስን፥ “ፈጽመህ ታዝናለህን?” አለው።
5ዮናስም ከከተማዪቱ ወጣ፤ በከተማዪቱም ፊት ለፊት#ዕብ. “በስተ ምሥራቅ በኩል” ይላል። ተቀመጠ፤ በከተማዪቱም የሚሆነውን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ። 6እግዚአብሔር አምላክም ቅልን አዘዘ፤ ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ራስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት፤ ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው። 7በነጋው ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘዘ፤ እርስዋም ቅሊቱን መታቻት፤ ደረቀችም። 8ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስን አዘዘ፤ ዮናስንም እስኪዝል ድረስ ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለራሱም ተስፋ ቈርጦ፥ “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” አለ። 9እግዚአብሔርም ዮናስን፥ “በውኑ ስለዚች ቅል ታዝናለህን?” አለው። እርሱም፥ “እስክሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ” አለ። 10እግዚአብሔርም፥ “አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት፥ ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። 11እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” አለው።
Currently Selected:
ትንቢተ ዮናስ 4: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in