የዮሐንስ ወንጌል 15
15
ጌታችን ኢየሱስ እውነተኛ የወይን ሐረግ ስለ መሆኑ
1“እውነተኛ የወይን ሐረግ እኔ ነኝ፤ ተካዩም አባቴ ነው። 2በእኔ ያለውን፥ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍም ሁሉ ያስወግደዋል፤ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን በብዙ እንዲያፈራ ያጠራዋል። 3እናንተ ግን ስለ ነገርኋችሁ ቃል ፈጽማችሁ ንጹሓን ናችሁ። 4በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። 5እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና። 6በእኔ የማይኖር ቢኖር እንደ ደረቅ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጥሉታል፤ ሰብስበውም በእሳት ያቃጥሉታል። 7በእኔም ብትኖሩ ቃሌም በእናንተ ቢኖር የምትሹትን ሁሉ ትለምናላችሁ፤ ይደረግላችሁማል። 8ብዙ ፍሬ ብታፈሩ፥ ደቀ መዛሙርቴም ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። 9አብ እንደ ወደደኝ እንዲሁ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬም ኑሩ። 10የምትወዱኝ ብትሆኑ ትእዛዜን ጠብቁ፤ እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ፥ በፍቅሩም እንደምኖር እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11ደስታዬ በእናንተ ይኖር ዘንድ፥ ደስታችሁም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን ነገርኋችሁ።
12 #
ዮሐ. 13፥34፤ 15፥17፤ 1ዮሐ. 3፥23፤ 2ዮሐ. 5። “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ እንድቷደዱ የእኔ ትእዛዝ ይህች ናት። 13ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ እንደ ሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም። 14እናንተስ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ካደረጋችሁ ወዳጆች ናችሁ። 15እንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ እናንተን ግን ወዳጆች እላችኋለሁ፤ በአባቴ ዘንድ የሰማሁትን ሁሉ ነግሬአችኋለሁና። 16እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ የመረጣችሁኝ አይደለም፤ እንድትሄዱ፥ ፍሬም እንድታፈሩ፥ ፍሬአችሁም እንዲኖር፤ አብንም በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ሁሉን እንዲሰጣችሁ ሾምኋችሁ። 17እርስ በርሳችሁም እንድቷደዱ ይህን አዝዣችኋለሁ።
ዓለም የጌታን ተከታዮች እንደሚጠላ
18“ዓለም ቢጠላችሁ አስቀድሞ እኔን እንደ ጠላ ዕወቁ። 19እናንተስ ከዓለም ብትሆኑ ዓለም በወደዳችሁ ነበር፤ ዓለም ወገኖቹን ይወዳልና፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ ከዓለም አይደላችሁምና ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። 20#ማቴ. 10፥24፤ ሉቃ. 6፥40፤ ዮሐ. 13፥16። እኔ፦ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም ያልኋችሁን ቃሌን ዐስቡ፤ እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ቢሆንስ ቃላችሁንም በጠበቁ ነበር። 21ነገር ግን ስለ ስሜ ይህን ሁሉ ያደርጉባችኋል፤ የላከኝን አያውቁትምና። 22ባልመጣሁና ባልነገርኋቸውስ ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው ምክንያት የላቸውም። 23እኔን የሚጠላ አባቴን ይጠላል። 24ሌላ ያልሠራውን ሥራ በመካከላቸው ባልሠራ ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፤ ጠልተውማል። 25ነገር ግን በኦሪታቸው፦ በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
መንፈስ ቅዱስ ከአብ ስለመሥረፁ
26“እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። 27እናንተም ትመሰክራላችሁ፤ ከጥንት ጀምሮ ከእኔ ጋር ኑራችኋልና።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 15: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in