ኦሪት ዘፍጥረት 32
32
ያዕቆብ ላባን ለመገናኘት እንደ ተዘጋጀ
1ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፤ በዐይኖቹም የእግዚአብሔርን ሠራዊት ከትመው አየ፤ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት። 2ያዕቆብም በአያቸው ጊዜ፥ “እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው” አለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም “ተዓይን” ብሎ ጠራው።
3ያዕቆብም ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም ሀገር በፊቱ መልእክተኞችን ላከ፤ 4እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ለጌታዬ ለዔሳው፦ ባሪያህ ያዕቆብ እንዲህ አለ ብላችሁ ንገሩት፦ በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ቈየሁ፤ 5ላሞችንም፥ ግመሎችንም፥ አህዮችንም፥ በጎችንም፥ ወንዶች አገልጋዮችንም፥ ሴቶች አገልጋዮችንም አገኘሁ፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለዔሳው ለመንገር ላክሁ።” 6የላካቸው መልእክተኞችም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት፥ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ።” 7ያዕቆብም እጅግ ፈራ፤ የሚያደርገውንም አጣ። ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች ላሞችንም፥ ግመሎችንም፥ በጎችንም ሁለት ወገን አድርጎ ከፈላቸው፤ 8ያዕቆብም እንዲህ አለ፥ “ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደ ሆነ የቀረው ወገን ይድናል።” 9ያዕቆብም አለ፥ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ ሆይ፥ ‘ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፤ በጎነትንም አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፥ 10ለባሪያህ በአደረግኸው በምሕረትህና በእውነትህም ሁሉ በጎውን አድርግልኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ። 11አቤቱ ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናትን#ዕብ. “እናቶችን ከልጆቻቸው ጋር” ይላል። ከልጆችዋ ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና። 12አንተም፦ ‘በርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር።’ ”
13በዚያችም ሌሊት በዚያው አደረ። ለወንድሙ ለዔሳውም የሚወስደውን እጅ መንሻ አወጣ፤ 14ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሃያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሃያ የበግ አውራዎችን፥ 15ሃምሳ#ዕብ. “ሠላሳ” ይላል። የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ ዐሥር በሬ፥ ሃያ እንስት አህያ፥ ዐሥርም የአህያ ውርንጫዎች፤ 16መንጎቹንም ለየብቻ ከፍሎ ለብላቴኖቹ ሰጣቸው፤ ብላቴኖቹንም፥ “በፊቴ እለፉ፤ መንጋውን ከመንጋው አርቁ” አላቸው።
17የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው፥ “ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደ ሆነ፦ ‘አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለሀ? በፊትህ ያለው ይህስ መንጋ የማን ነው?’ ብሎ የጠየቀህም እንደሆነ፥ 18በዚያ ጊዜ አንተ፦ ‘ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የላከው የአገልጋይህ የያዕቆብ ነው፤ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ተከትሎናል’ በለው።” 19እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን፥ በፊቱ የሚሄዱትንና መንጋውን የሚነዱትን ሁሉ እንዲሁ ብሎ አዘዘ፦“ ወንድሜ ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤ 20እንዲህም በሉ፦ እነሆ አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው። በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል፤ ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና።” 21እጅ መንሻውን ከእርሱ አስቀድሞ ላከ፤ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት በሰፈር አደረ።
የያዕቆብ ትግል
22በዚያችም ሌሊት ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ዕቁባቶቹን ዐሥራ አንዱንም ልጆቹን ይዞ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። 23ወሰዳቸውም፤ ወንዙንም አሻገራቸው፤ ገንዘቡንም ሁሉ አሻገረ። 24ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር። 25እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ያዘው፤ የያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ። 26እንዲህም አለው፥ “ሊነጋ ጎሕ ቀድዶአልና ልቀቀኝ።” እርሱም “ከአልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው። 27እንዲህም አለው፥ “ስምህ ማን ነው?” እርሱም፥ “ያዕቆብ ነኝ” አለው። 28አለውም፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ታግለህ በርትተሃልና።” 29ያዕቆብም፥ “ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፥ “ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? ድንቅ ነውና”#“ድንቅ ነውና” በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. የለም። አለው። 30በዚያም ስፍራ ባረከው። ያዕቆብም፥ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፤ ሰውነቴም ዳነች” ሲል የዚያን ቦታ ስም “ራእየ እግዚአብሔር” ብሎ ጠራው። 31ራእየ እግዚአብሔርንም በተወ ጊዜ ፀሐይ ወጣችበት። እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። 32ስለዚህም የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን ሹልዳ አይበሉም፤ የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርቹን ሹልዳ አደንዝዞአልና።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 32: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in