ኦሪት ዘፍጥረት 17
17
ግዝረት የቃል ኪዳን ምልክት ሆኖ መሰጠቱ
1ከዚህም በኋላ አብራም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው “በፊትህ የሄድሁ ፈጣሪህ#“በፊትህ የሄድሁ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. የለም። እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ በፊቴ መልካም አድርግ፤ ንጹሕም ሁን፤ 2ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አጸናለሁ፤ እጅግም አበዛሃለሁ።” 3አብራምም በግንባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም አብራምን እንዲህ አለው፦ 4“እነሆ፥ ቃል ኪዳኔን በእኔና በአንተ መካከል አጸናለሁ፤ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። 5እንግዲህ ስምህ አብራም አይባልም ‘አብርሃም’ ይባላል እንጂ፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። 6እጅግም በጣም አበዛሃለሁ፤ ሕዝብም፥ ነገሥታትም ከአንተ እንዲወጡ አደርግሃለሁ። 7ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል በትውልዳቸው ለዘለዓለም ኪዳን አቆማለሁ፤ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። 8በውስጥዋ የምትኖርባትን ይህችን ምድር፥ የከነዓንን ምድር ሁሉ፥ ለዘለዓለም ይገዙአት ዘንድ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ።”
9እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ “አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፤ አንተ፥ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። 10በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቋት ቃል ኪዳኔ ይህች ናት፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። 11የሰውነታችሁን ቍልፈት ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። 12ሕፃኑንም በስምንተኛው ቀን ትገርዙታላችሁ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ፥ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ። 13በቤትህም የተወለደ፥ በብርም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ።#በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. ብቻ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆናል። 14በስምንተኛው ቀን የሥጋውን ቍልፈት ያልተገረዘ፥ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፤ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና።”
15እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ “ሚስትህ ሦራ እንግዲህ ሦራ ተብላ አትጠራም፤ ስምዋ ‘ሣራ’ ይሆናል እንጂ። 16እባርካታለሁና፥ ከአንተም ልጆችን እሰጣታለሁና፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከእርስዋ ልጆች እሰጥሀለሁ” ይላል። አሕዛብና የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ ይወጣሉ።”#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እባርካታለሁ ከእርስዋም ልጅን እሰጥሃለሁ እባርከውማለሁ ሕዝብም ይሆናል የአሕዛብ ነገሥታትም ከእርሱ ይወጣሉ” ይላል። 17አብርሃምም በግንባሩ ወደቀ፤ ሳቀም፤ በልቡም እንዲህ ብሎ አሰበ፥ “የመቶ ዓመት ሰው ስሆን በውኑ እኔ ልጅ እወልዳለሁን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን?” 18አብርሃምም እግዚአብሔርን አለው፥ “ይህ ይስማኤል ብቻ በፊትህ ይኖርልኝ ዘንድ አቤቱ፥ እማልድሃለሁ።” 19እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ “እሺ እነሆ፥ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ለእርሱና ከእርሱ በኋላ ለዘሩ አምላክ እሆን ዘንድ ቃል ኪዳኔን ለዘለዓለም ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። 20ስለ ይስማኤልም እነሆ፥ ሰምቼሃለሁ፤ እባርከዋለሁ፤ አበዛዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ ዐሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፤ ታላቅ ሕዝብም አደርገዋለሁ። 21ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ።”
22እግዚአብሔርም ንግግሩን ከእርሱ ጋር በፈጸመ ጊዜ ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ። 23አብርሃምም ልጁን ይስማኤልን፥ በቤቱም የተወለዱትን ሁሉ፥ በወርቅም የገዛውን ወንድ ሁሉ፥ ከቤተ ሰቡም ወንዶቹን ሁሉ ወሰደ። የሥጋቸውንም ቍልፈት እግዚአብሔር እንዳለው በዚያው ቀን ገረዘ። 24አብርሃምም የሥጋውን ቍልፈት በተገረዘ ጊዜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሆኖት ነበረ፤ 25ልጁ ይስማኤልም የሥጋውን ቍልፈት በተገረዘ ጊዜ ዐሥራ ሦስት ዓመት ሆኖት ነበረ። 26በዚያም ቀን አብርሃም ተገረዘ፤ ልጁ ይስማኤልም። 27በቤት የተወለዱትና በብር ከእንግዶች የተገዙት፥ የቤቱ ወንዶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 17: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in