ትንቢተ ሕዝቅኤል 3
3
1እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ያገኘኸውን ብላ፤#“ያገኘኸውን ብላ” የሚለው በዕብ. ብቻ። ይህን መጽሐፍ ብላ፤ ሄደህም ለእስራኤል ልጆች ተናገር” አለኝ። 2አፌንም ከፈትሁ፤ መጽሐፉንም አበላኝ። 3እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! አፍህ ይብላ፤ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ።
4እንዲህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድና ግባ፥ ቃሌንም ንገራቸው። 5ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ልዩ ወደ ሆነ፥ ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህምና፤ 6ንግግራቸው ልዩ ወደ ሆነ፥ ቋንቋቸውም ሌላ ወደ ሆነ፥ ቃላቸውንም ታውቅ ዘንድ ወደማይቻልህ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነዚያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰሙህ ነበር። 7ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ ክፉዎችና ልበ ደንዳኖች ናቸውና፥ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙህም። 8እነሆ ፊትህን በፊታቸው አጸናሁት፤ ኀይልህንም ከኀይላቸው ይልቅ አጸናለሁ። 9ሁልጊዜ ከዓለት ይልቅ ትጸናለህ፤ አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም አትደንግጥ፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና።”#ዕብ. “ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንደ አልማዝ ግንባርህን አጠንክሬአለሁ” ይላል።
10እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! የነገርሁህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ጠብቀው፤ በጆሮህም ስማው። 11ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፤ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ቢፈሩ፦#ዕብ. “ባይሰሙ” ይላል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው” አለኝ። 12መንፈስም ወደ ላይ ወሰደኝ፤ በኋላዬም፥ “የእግዚአብሔር ክብር ከቦታው ይባረክ” የሚል የታላቅ ንውጽውጽታ ድምፅ ሰማሁ። 13የእነዚያም እንስሳ ክንፎች እርስ በርሳቸው ሲማቱ፥ በአጠገባቸውም የመንኰራኵሮችን ድምፅ፥ የታላቁንም ንውጽውጽታ ድምፅ ሰማሁ። 14መንፈስም አንሥቶ ወሰደኝ፤ እኔም በምሬትና#“በምሬትና” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በመንፈሴ ሙቀት ሄድሁ፤ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ በርትታ ነበር። 15በቴልአቢብም#“በቴልአቢብም” የሚለው በግእዝ እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ወደ አሉ፥ በኮቦርም ወንዝ አጠገብ ወደ ተቀመጡ ምርኮኞች መጣሁ፤ በተቀመጡበትም ቦታ ተቀመጥሁ፤ በዚያም በመካከላቸው እየተመላለስሁ ሰባት ቀን ተቀመጥሁ።
እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን ጠባቂ አድርጎ እንደ ሾመው
16ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 17“የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ፤ በቃሌም ገሥጻቸው። 18እኔ ኀጢአተኛውን፥ “በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ አንተም ባትነግረው፥ ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኀጢአተኛው ባትነግረው፥ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱ ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 19ነገር ግን አንተ ኀጢአተኛውን ብትገሥጸው እርሱም ከኀጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ። 20ደግሞ ጻድቁ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት በሠራ ጊዜ እኔ በፊቱ ዕንቅፋት ባደርግ፥ እርሱ ይሞታል፤ አንተም አልነገርኸውምና በኀጢአቱ ይሞታል፤ ያደረጋትም የጽድቅ ነገር አትታሰብለትም፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 21ነገር ግን ኀጢአት እንዳይሠራ ጻድቁን ብትገሥጸው፥ እርሱም ኀጢአት ባይሠራ፥ ጻድቅ ነውና በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን አድነሃል።”
22በዚያም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፤ እርሱም፥ “ተነሥተህ ወደ ሜዳ ሂድ፤ በዚያም እነግርሃለሁ” አለኝ። 23እኔም ተነሥቼ ወደ ሜዳው ሄድሁ፤ እነሆም በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ክብር ያለ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፤ በግምባሬም ተደፋሁ። 24መንፈስም ወደ እኔ መጣ፤ በእግሬም አቆመኝ፤ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ፥ “ሂድ ገብተህ ቤትህን ዝጋ። 25አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ! እነሆ ገመድ ያደርጉብሃል፤ ያስሩህማል፤ አንተም ከመካከላቸው አትወጣም፤ 26እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ፤ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም። 27ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚሰማ ይስማ፤ እንቢ የሚልም እንቢ ይበል” ትላቸዋለህ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 3: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in