ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1
1
በኤፌሶን ስላሉ ምእመናን
1 #
የሐዋ. 18፥19-21። በእግዚአብሔር ፈቃድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ ከጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ በኤፌሶን ላሉ ቅዱሳን፥ 2ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።
በረከትና ምስጋና
3በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን። 4ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን፥ ንጹሓንና ያለ ነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን። 5በኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ውድ ፈቃዱ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። 6በሚወደው ልጁ የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ። 7#ቈላ. 1፥14። በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፤ ኀጢአታችንም ተሰረየልን። 8ይኸውም በፍጹም ጥበብና ምክር ለእኛ አብዝቶ ያደረገው ነው። 9እንደ ወደደም በእርሱ የወሰነውን፥ የፈቃዱን ምሥጢር ገለጠልን። 10የሚደርስበትንም ጊዜውን ወሰነ፤ በሰማይና በምድር ያለውም ሁሉ ይታደስ ዘንድ ክርስቶስን በሁሉ ላይ አላቀው። 11እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ አስቀድመን የተወሰን በእርሱ ርስትን ተቀበልን። 12ይኸውም አስቀድመን በክርስቶስ ኢየሱስ ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። 13እናንተም ልትድኑበት የተማራችሁትን የእውነት ቃል ሰምታችሁና አምናችሁ፤ ተስፋ ባደረገላችሁ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ። 14ይኸውም ለጌትነቱ ክብር የርስታችን መያዣ፥ የሕይወታችንም ቤዛነት ነው።
ምእመናንን ስለ ማሰብ
15ስለዚህም እኔ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናችሁን፥ ቅዱሳንንም ሁሉ መውደዳችሁን ሰምቼ፥ 16ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ማመስገንንና በጸሎቴም እናንተን ማሰብን አላቋረጥሁም። 17ይኸውም የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ እግዚአብሔር የጥበብን መንፈስ ይሰጣችሁ ዘንድ፥ ዕውቀቱንም ይገልጽላችሁ ዘንድ፥ 18ዐይነ ልቡናችሁንም ያበራላችሁ ዘንድ፥ የተጠራችሁበት ተስፋም ምን እንደ ሆነ፥ በቅዱሳንም የርስቱ ክብር ባለጸግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ፥ 19በክርስቶስ እንደ አደረገው እንደ ከሃሊነቱ ታላቅነት በምናምን በእኛ ላይ የሚያደርገው የከሃሊነቱ ጽናት ብዛት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ ነው። 20#መዝ. 109፥1። ከሙታን ለይቶ ባስነሣው፥ በሰማይም በቀኙ ባስቀመጠው፥ 21ከመላእክት ሁሉ በላይ ከመኳንንትና ከኀይላት፥ ከአጋእዝትና ከሚጠራውም ስም ሁሉ በላይ፥ በዚህ ዓለም ብቻ አይደለም፤ በሚመጣውም ዓለም እንጂ። 22#መዝ. 8፥6። ሁሉንም ከእግሩ በታች አድርጎ አስገዛለት፤ ከሁሉ በላይ የሆነ እርሱን ለቤተ ክርስቲያን ራስ አደረገው። 23#ቈላ. 1፥18። ይህችውም አካሉ ናት፤ የሁሉም ፍጻሜው እርሱ ነው፤ ሁሉንም በሁሉ ይፈጽማል።
Currently Selected:
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in