የሐዋርያት ሥራ 7
7
የእስጢፋኖስ ምስክርነት
1ሊቀ ካህናቱም፥ “በእውነት እንዲህ ብለሃልን?” አለው። 2እርሱም እንዲህ አለ፥ “ወንድሞቻችንና አባቶቻችን ሆይ፥ ስሙ፤ የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ወደ ካራንም ሳይመጣ ተገለጠለት። 3#ዘፍ. 12፥1። ‘ካገርህ ውጣ፤ ከዘመዶችህም ተለይ፤ እኔም ወደማሳይህ ሀገር ና’ አለው። 4#ዘፍ. 11፥31፤ 12፥4። ከዚህም በኋላ ከከለዳውያን ሀገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ፤ ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ፥ ዛሬ እናንተ ወደ አላችሁባት ወደዚች ሀገር አመጣው። 5#ዘፍ. 12፥7፤ 13፥15፤ 15፥18፤ 17፥8። በውስጥዋም አንድ ጫማ ታህል ስንኳን ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን እርሱ ከእርሱም በኋላ ዘሩ ሊገዛት ልጅ ሳይኖረው ያንጊዜ እርስዋን ያወርሰው ዘንድ ተስፋ ሰጠው። 6#ዘፍ. 15፥13-14። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ ‘ዘርህ በባዕድ ሀገር መጻተኞች ሆነው ይኖራሉ፤ አራት መቶ ዓመትም ባሮች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ መከራም ያጸኑባቸዋል። 7#ዘፀ. 3፥12። ደግሞም እግዚአብሔር አለ፤ ባሮች አድርገው በሚገዙአቸው ወገኖች እኔ እፈርድባቸዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ፤ በዚህም ሀገር ያመልኩኛል።’ 8#ዘፍ. 17፥10-14፤ 21፥2-4፤ 25፥26፤ 29፥31—35፥18። የግዝረትንም ኪዳን ሰጠው፤ ከዚህም በኋላ ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛው ቀንም ገረዘው፤ እንዲሁ ይስሐቅም ያዕቆብን፥ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የቀደሙ አባቶችን ገረዙ።
ስለ ዮሴፍ
9 #
ዘፍ. 37፥11፤ 28፤ 39፥2፤ 21። “የቀደሙ አባቶችም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብፅ ሀገር ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበረ። 10#ዘፍ. 41፥39-41። ከመከራውም ሁሉ አዳነው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፤ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይ ቢትወደድ አድርጎ ሾመው። 11#ዘፍ. 42፥1-2። በግብፅና በከነዓን ሀገር ሁሉ ረኃብና ታላቅ ጭንቅ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉት አጡ። 12ያዕቆብም በግብፅ ሀገር እህል እንዳለ ሰማ፤ አባቶቻችንንም አስቀድሞ ላካቸው። 13#ዘፍ. 45፥1፤ 16። ወደ ግብፅም እንደ ገና በተመለሱ ጊዜ ወንድሞቹ ዮሴፍን ዐወቁት፤ ፈርዖንም የዮሴፍን ዘመዶች ዐወቃቸው። 14#ዘፍ. 45፥9-10፤17-18፤ 46፥27። ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ እንዲጠሩአቸው ላከ፤ ቍጥራቸውም ሰባ አምስት ነፍስ ነበር።
ያዕቆብ ወደ ግብፅ ስለ መውረዱ
15 #
ዘፍ. 46፥1-7፤ 49፥33። “ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ፥ እርሱም አባቶቻችንም ሞቱ። 16#ዘፍ. 23፥3-16፤ 33፥19፤ 50፥7-13፤ ኢያ. 24፥32። ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በገንዘቡ በገዛው መቃብር ቀበሩዋቸው።
17 #
ዘፀ. 1፥7-8። “እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን በደረሰ ጊዜ እስራኤል በዙ፤ የግብፅንም ሀገር መሉ። 18ይህም ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ እስከ ነገሠ ድረስ ነበር። 19#ዘፀ. 1፥10-11፤ 22። እርሱም ወገኖቻችንን ተተንኵሎ አባቶቻችንን መከራ አጸናባቸው፤ ወንድ ልጅንም ሁሉ እንዲገድሉ አዘዘ።
ስለ ሙሴ
20 #
ዘፀ. 2፥2። “ያንጊዜም ሙሴ ተወለደ፤ በእግዚአብሔር ፊትም የተወደደ ሆነ፤ ለሦስት ወርም በአባቱ ቤት አሳደጉት። 21#ዘፀ. 2፥3-10። በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው፤ ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው። 22ሙሴም የግብፅን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በሚናገረውና በሚሠራውም ሁሉ ብርቱ ሆነ።
23 #
ዘፀ. 2፥11-15። “አርባ ዓመት ሲሞላውም ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኛቸው በልቡ ዐሰበ። 24አንድ ግብፃዊም ዕብራዊውን ሲበድለው አገኘና ለዚያ ለተበደለው ረድቶ ግብፃዊውን ገደለው በአሸዋም ቀበረው።#“በአሸዋ ቀበረው” የሚለው በግሪኩ የለም። 25እርሱም እግዚአብሔር በእጁ ድኅነትን እንደሚያደርግላቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። 26በማግሥቱም ከመካከላቸው ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኘ፤ ሊያስታርቃቸውም ወድዶ፦ ‘እናንተማ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ለምን ትጣላላችሁ?’ አላቸው። 27ያም ባልንጀራውን የሚበድለው ገፋው፤ እንዲህም አለው፦ ‘አንተን በእኛ ላይ ዳኛና ፈራጅ አድርጎ ማን ሾመህ? 28ወይስ ትናንትና ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትሻለህን?’ 29#ዘፀ. 18፥3-4። ስለዚህም ነገር ሙሴ ኮብልሎ በምድያም ሀገር ስደተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆችን ወለደ።
30 #
ዘፀ. 2፥14። “አርባ ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ በበረሃ በደብረ ሲና የእግዚአብሔር መልአክ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው። 31ሙሴም አይቶ በአየው ተደነቀ፤ ሊያስተውለውም ቀረበ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው። 32‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤’ ሙሴም ተንቀጠቀጠ፤ መረዳትም አልቻለም። 33እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ ‘ጫማህን ከእግርህ አውልቅ፤ የቆምህባት ምድር የተቀደሰች ናትና። 34በግብፅ ያሉትን የወገኖችን መከራ ማየትን አይቻለሁ፤ ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ፤ አሁንም ና ወደ ግብፅ ሀገር ልላክህ።’
ሙሴ ወደ ግብፅ ስለ መላኩ
35“በእኛ ላይ አለቃና ፈራጅ ማን አድርጎሃል? ብለው የካዱትን ያን ሙሴን በቍጥቋጦው መካከል በታየው በመልአኩ እጅ እርሱን መልእክተኛና አዳኝ አድርጎ እግዚአብሔር ላከው። 36#ዘፀ. 7፥5፤ 14፥21፤ ዘኍ. 14፥33። እርሱም አርባ ዘመን በግብፅ ሀገርና በኤርትራ ባሕር፥ በበረሃም ተአምራትንና ድንቅ ሥራን እየሠራ አወጣቸው። 37#ዘዳ. 8፥15፤ 18። ለእስራኤልም ልጆች፦ ‘እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋልና እርሱን ስሙት’ ያላቸው ይህ ሙሴ ነው። 38#ዘፀ. 19፥1—20፥17፤ ዘዳ. 5፥1-33። በምድረ በዳ በማኅበሩ መካከል የነበረ እርሱ ነው፤ በደብረ ሲና ከአነጋገረው መልአክና፤ ከአባቶቻችንም ጋር ለእኛ ሊሰጠን የሕይወትን ቃል የተቀበለ እርሱ ነው። 39አባቶቻችን ለእርሱ መታዘዝን እንቢ አሉ፤ ከዱትም፤ ልባቸውንም ወደ ግብፅ ሀገር መለሱ። 40#ዘፀ. 32፥1። አሮንንም፦ ‘በፊት በፊታችን የሚሄዱ አማልክትን ሥራልን፤ ያ ከምድረ ግብፅ ያወጣን ሙሴ የሆነውን አናውቅምና’ አሉት። 41#ዘፀ. 32፥2-6። ያንጊዜም የጥጃ ምስል ሠሩ፤ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸው ሥራም ደስ አላቸው። 42እግዚአብሔርም ተለያቸው፤ የሰማይ ጭፍራን ያመልኩም ዘንድ ተዋቸው፤ የነቢያት መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ፤ ‘እናንት የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ በውኑ በምድረ በዳ ሳላችሁ አርባ ዐመት ያቀረባችሁልኝ ቍርባንና መሥዋዕት አለን? 43#አሞ. 5፥25-27። ነገር ግን የሞሎህን ድንኳን አነሣችሁ፤ ሬፋን የሚባለውንም ኮከብ አመለካችሁ፤ ትሰግዱላቸውም ዘንድ ምስሎቻቸውን አበጃችሁ፤ እኔም ወደ ባቢሎን እንድትማረኩ አደርጋችኋለሁ።’
44 #
ዘፀ. 25፥9፤ 40። “ሙሴን ተናግሮ እንደ አዘዘው በአሳየው ምሳሌ የሠራት የምስክር ድንኳን በአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች። 45#ኢያ. 3፥14-17። ኢያሱና አባቶቻችንም በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ፊት አስወጥቶ ወደ ሰደዳቸው ወደ አሕዛብ ሀገር ከእነርሱ ጋር አገቡአት፤ እስከ ዳዊት ዘመንም ነበረች። 46#2ሳሙ. 7፥1-16፤ 1ዜ.መ. 17፥1-14። ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ባለመዋልነትን አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ያገኝ ዘንድ ለመነ። 47#1ነገ. 6፥1-38፤ 2ዜ.መ. 3፥1-17። ሰሎሞን ግን ቤትን ሠራለት። 48ነገር ግን ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት የሚኖር አይደለም፤ ነቢይ እንዲህ ብሎአልና። 49እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? የማርፍበት ቦታስ ምን ዐይነት ቦታ ነው? 50#ኢሳ. 66፥1-2። ይህን ሁሉ እጆች የሠሩት አይደለምን?’
ስለ እስጢፋኖስ የመጨረሻ ንግግር
51 #
ኢሳ. 63፥10። “እናንተ አንገታችሁ የደነደነ፥ ልባችሁም የተደፈነ፥ ጆሮአችሁም የደነቈረ፥ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ዘወትር ትቃወማላችሁ። 52አባቶቻችሁ ከነቢያት ያላሳደዱት ማን አለ? ዛሬም እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና የገደላችሁትን የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሉአቸው። 53በመላእክትም ሥርዐት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁትም።”
የእስጢፋኖስ በድንጋይ መገደል
54ይህንም ሰምተው ተበሳጩ፤ ልባቸውም ተናደደ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። 55በእስጢፋኖስም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላ፤ ወደ ሰማይም ተመለከተ፤ የእግዚአብሔርን ክብር፥ ኢየሱስም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ተቀምጦ” ይላል። አየ። 56“እነሆ ሰማይ ተከፍቶ፤ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ተቀምጦ” ይላል። አያለሁ” አለ። 57እነርሱም በታላቅ ቃል ጮኹ፤ ጆሮአቸውንም ደፈኑ፤ በአንድነትም ተነሥተው ከበቡት። 58ከከተማም ወደ ውጭ ጐትተው አውጥተው ወገሩት፤ የሚወግሩት ሰዎችም ልብሳቸውን ሳውል በሚባል ጐልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ።#ግሪኩና አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ምስክሮች ልብሳቸውን ... አስጠበቁ” ይላል። 59እስጢፋኖስም፥ “ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል” እያለ ሲጸልይ ይወግሩት ነበር። 60በጕልበቱም ተንበርክኮ፥ “አቤቱ፥ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ ሞተ፤ ሳውልም በእስጢፋኖስ ሞት ተባባሪ ነበር።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 7: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in