YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ጢሞ​ቴ​ዎስ 2 4

4
1በእግዚአብሔር ፊት፥ በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ 2ቃሉን ስበክ፤ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፤ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ ዝለፍና ገሥጽ፤ ምከርም። 3ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።
ጳውሎስ የጽድቅን አክሊል ለመቀዳጀት ተስፋ እንዳደረገ
4እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ። 5አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፤ አገልግሎትህን ፈጽም።
6በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል። 7መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፤ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፤ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ 8ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።
ስለ ግል ጉዳዮች
9በቶሎ ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ፤ 10ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል፤ ቄርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል። 11ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ፤ ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው። 12ቲኪቆስን ግን ወደ ኤፌሶን ላክሁት። 13ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ። 14የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ እጅግ ከፋብኝ፤ ጌታ እንደ ሥራው ይመልስለታል። 15አንተም ደግሞ ከእርሱ ተጠበቅ፤ የምንናገረውን እጅግ ተቃውሞአልና። 16በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፤ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤ 17ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፤ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ። 18ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
የመጨረሻ ሰላምታ
19ለጵርስቅላና ለአቂላ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ። 20ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀረ፤ ጥሮፊሞስን ግን ታሞ በሚሊጢን ተውሁት። 21ከክረምት በፊት እንድትመጣ ትጋ። ኤውግሎስና ጱዴስ ሊኖስም ቅላውዲያም ወንድሞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።
22ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in