ወደ ሮሜ ሰዎች 1
1
ሰላምታ
1የክርስቶስ ኢየሱስ ባርያ ጳውሎስ፥ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፥ 2ይህም ወንጌል እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያቱ አማካኝነት በቅዱሳን መጻሕፍት የሰጠው ተስፋ ነው፤ 3ወንጌሉም ስለ ልጁ፥ በሥጋ ከዳዊት ዘር እንደመጣ፥ 4ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስና መንፈስ ከሙታን በመነሣት በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ መገለጡ ነው፤ 5ስለ ስሙ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ለእምነት መታዘዝን ለማምጣት ጸጋና ሐዋርያነትን በተቀበልንበት በእርሱ በኩል፥ 6የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ በተጠራችሁ በእናንተም መካከል፥ 7በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁ፥ በሮሜ ላላችሁ ሁሉ፥ ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ጳውሎስ ሮሜን ለማየት የነበረው ምኞት
8እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ስለ ሁላችሁም በመጀመሪያ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። 9ያለማቋረጥ እንዴት እንደማስባችሁ የልጁን ወንጌል በመስበክ በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ 10ምናልባት አሁን በመጨረሻ፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ ለመምጣት ሁልጊዜ በጸሎቴ እጠይቃለሁ። 11የሚያጸናችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁ፤ 12ይህም እርስ በእርሳችን በእናንተና በእኔ ዘንድ ባለች እምነት፥ አብረን እንድንጽናና ነው። 13#የሐዋ. 19፥21።ወንድሞች ሆይ! በሌሎቹ ሕዝቦች እንዳገኘሁት በእናንተም ፍሬ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንዳቀድሁ እስከ አሁን ግን እንደ ተከለከልሁ እንድታውቁ እወዳለሁ። 14ለግሪኮችና ግሪኮች ላልሆኑት፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉትም ዕዳ አለብኝ፤ 15ስለዚህ በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ እጓጓለሁ።
የወንጌሉ ኃይል
16 #
ማር. 8፥38። በወንጌል አላፍርምና፤ በመጀመሪያ ለአይሁድ እንዲሁም ለግሪካውያን፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው። 17#ዕን. 2፥4።“ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና።
የሰው ልጆች ዐመፅ
18በክፋታቸው እውነትን አፍነው በሚይዙ ሰዎች፥ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤ 19ስለ እግዚአብሔር መታወቅ የሚገባው በእነርሱ መካከል ግልፅ ነው፤ ምክንያቱም ለእነርሱ እግዚአብሔር ግልፅ አድርጎላቸዋል። 20#ጥበ. 13፥1-9፤ ሲራ. 17፥8።ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታዩት ነገሮች፥ ይኸውም ዘላለማዊው ኃይሉና መለኮታዊነቱ ታውቆ፥ ግልፅም ሆኖ ስለሚታይ ሰበብ የላቸውም። 21#ኤፌ. 4፥17፤18።ምክንያቱም እግዚአብሔርን እያወቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን አላከበሩትም ወይም አላመሰገኑትም፤ ነገር ግን ምክንያታቸው ዋጋ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ። 22ጥበበኞች ነን ሲሉ ሞኞች ሆኑ፤ 23#ዘዳ. 4፥16-18፤ ጥበ. 11፥15፤ 12፥24፤ 13፥10-19።የማይጠፋውን የእግዚአብሔርን ክብር በሚጠፋው በሰው፥ በወፎች፥ አራት እግር ባላቸው እንስሳትና በመሬት ላይ በሚሳቡ እንስሳት መልክ ምስል ለወጡ። 24ስለዚህ እግዚአብሔር እርስ በእርሳቸው ሥጋቸውን እንዲያዋርዱ፥ በልባቸው ፍትወት ለርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ 25የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን አመለኩ አገለገሉትም፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተባረከ ነው፤ አሜን።
26በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ለሚያዋርድ ፍትወት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ተፈጥሮአዊውን ግንኙነት ተፈጥሮአዊ ባልሆነ ግንኙነት ለወጡ፤ 27እንዲሁም ደግሞ ወንዶች ተፈጥሮአዊ የሆነውን ከሴት ጋር መገናኘት ትተው እርስ በእርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ፤ በስሕተታቸውም ምክንያት የሚገባቸውን ቅጣት በራሳቸው ላይ ተቀበሉ። 28እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈለጉ እግዚአብሔር ተገቢ ያልሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ 29በዐመፃ፥ በግፍ፥ በስስት፥ በክፋት፥ በቅናት፥ ነፍስ በመግደል፥ በጥል፥ በአታላይነት፥ በተንኮል የተሞሉ፥ የሚያሾከሹኩ፥ 30ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚዳፈሩ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚያውጠነጥኑ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ 31የማያስተውሉ፥ የማይታመኑ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት የሌላቸው ናቸው፤ 32“እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉ ሞት ይገባቸዋል” የሚለውን ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ሕግ ቢያውቁም፥ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ እንዲህ የሚያደርጉትንም ያበረታታሉ።
Currently Selected:
ወደ ሮሜ ሰዎች 1: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in