YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ምሳሌ መግቢያ

መግቢያ
መጽሐፈ ምሳሌ የምክሮችና የአባባሎች ስብስብ ሲሆን የመጽሐፉም ዓላማ ጥበብን ማስተማር ነው። ጥበብም የሚመለከተው ሐሳብንና እውቀትን ብቻ ሳይሆን ተግባርን፥ የሕይወት ልምምድን፥ ሙያንና ጸባይንም ጭምር ነው። የጥበብ ባለቤትና ምንጭ አምላክ መሆኑንና ሰዎችም ጥበብን ከአምላክ እንደሚቀበሉ ያስተምራል። እንደ ምሳሌ 16፥12-15 አስተምህሮ ነገሥታት፥ ጻፎችና የቤተሰብ ኃላፊዎች (ምሳሌ 1፥1-7) በአግባቡ የሚሠሩትና የሚያስተዳድሩት ከእግዚአብሔር በሚቀበሉት ጥበብ ነው። የጥበብ ጉዳይ ከመጽሐፈ መክብብና ከመጽሐፈ ኢዮብ ይልቅ በመጽሐፍ ምሳሌ ውስጥ በሰፊው ተተንትኗል። ለጥበብ የተሰጠው ትኩረት ከሚታይባቸው መንገዶች አንዱ በምሳሌያዊና በዘይቤያዊ ንግግር ጥበብን መግለጽ ነው። በዚህም መሠረት፥ በሰውኛ ዘይቤ፥ ጥበብ በአንዲት እመቤት ተመስላ ቀርባለች። እመቤት ጥበብ ሰዎች ጥበብን እንዲፈልጉ ትጋብዛለች። ሰው በግሉ ወይንም በራሱ ምንም ቢጥር ከጥበብ የሚገኘውን ጸጋ የሚተካካል እውቀትና አቅም ማግኘት አይችልም። ለሰው ልጅ ትልቁ የሕይወት ምርጫ የጥበብን ጎዳና መከተል ነው። ምንም እንኳን የጥበብ ጉዳናን የሚመርጥ ሰው ብዙ መሰናክል ቢገጥመውም፥ በማስተዋል ፈተናዎችን መወጣት ይችላል። ጥበብ ከእግዚአብሔር ስለሚሰጥ፥ ሰው ልቡን ወደ ጥበብ ሊያዘነብል ይገባዋል። ጥበብን ለማግኘት ረጋ ማለትና ማስተዋል ያስፈልጋል።
በክርስትና እይታ ክርስቶስ ከአብ የተላክ የእግዚአብሔር ጥበብ ሲሆን፥ ለሰዎች እውነተኛና ሙላት ያለውን ሕይወት ይሰጣል። የክርስቶስም ትምህርት የጥበብ ትምህርት እንደሆነ የያዕቆብ መልክትም ይዘረዝራል።
በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ ዘጠኝ ንኡስ ክፍሎችን ማየት ይቻላል።
1. ርእስና መግቢያ (1፥1-7)
2. የወላጆች እና የ “እመቤት ጥበብ” ምክር (1፥8—9፥18)
3. የሰለሞን ምሳሌዎች (10፥1—22፥16)
4. የጠቢባን ምሳሌዎች (22፥17—24፥22)
5. ተጨማሪ የጠቢባን ምሳሌዎች (24፥23-34)
6. ተጨማሪ የሰለሞን ምሳሌዎች (25፥1—29፥27)
7. የአጉርና የሌሎች ጠቢባን ምሳሌዎች ኤሊሁ ንግግር (30፥1-33)
8. የንጉሥ ልሙኤል ምሳሌዎች (31፥1-9)
9. የመልካም ሴት ክብር (31፥10-31)
ምዕራፍ

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in