YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ምሳሌ 3

3
1ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥
ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።
2ብዙ ቀኖች፥ የሕይወት ዓመታትና
ሰላምም ይጨምሩልሃልና።
3ደግነትና እውነት አይተዉህ፥
በአንገትህ ላይ እሰራቸው፥
በልብህ ጽላት ጻፋቸው።
4 # ሉቃ. 2፥52። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም
ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።
5በፍጹም ልብህ በጌታ ታመን፥
በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፥
6በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥
እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።
7 # ሮሜ 12፥16። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፥
ጌታን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፥
8ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፥
ለአጥንትህም መታደስ።
9ከሀብትህ አስበልጠህ ጌታን አክብር፥
ከፍሬህም ሁሉ በኵራት ይልቅ፥
10ጐተራህም እህልን ይሞላል፥
መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች።
11 # ኢዮብ 5፥17፤ ዕብ. 12፥5፤6። ልጄ ሆይ፥ የጌታን ተግሣጽ አትናቅ፥
በገሠጸህም ጊዜ አትመረር።
12 # ራእ. 3፥19። ጌታ የወደደውን ይገሥጻልና፥
አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ።
13ጥበብን የሚያገኝ ሰው ብጹዕ ነው፥
ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ ሰው፥
14በእርሷ የሚገኘው ትርፍ ከብር ከሚገኘው፥ ገቢዋም ከወርቅ ይሻላልና።
15ከውድ ዕንቁም ትከብራለች፥
ከምትመኘው ነገር አንዳችም አይተካከላትም።
16በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፥
በግራዋም ባለጠግነትና ክብር#3፥16 ወደ እርሷ ለሚምጡ ጥበብ በሁለቱም እጆችዋ ብዙ እንደምትለግስ ለማሳየት ነው።
17መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፥
ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው።
18እርሷ ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፥
የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው።
19ጌታ በጥበብ ምድርን መሠረተ፥
በማስተዋልም ሰማያትን አጸና።
20በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፥
ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
21ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዐይኖችህ አይራቁ፥
መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ።
22ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥
ለአንገትህም ሞገስ።
23የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥
እግርህም አይሰነካከልም።
24በተኛህ ጊዜ አትፈራም፥
ስትተኛም፥ እንቅልፍህ የጣፈጠ ይሆንልሃል።
25ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥
ከሚመጣውም ከኀጥኣን ጥፋት አትፈራም፥
26ጌታ መታመኛህ ይሆናልና፥
እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና።
27 # ሲራ. 4፥3። ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን፥
ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ከማድረግ አትቆጠብ።
28በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ፥
ወዳጅህን፦ “ሂድና ተመለስ፥ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው።
29እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ፥
በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ።
30እርሱ ክፉ ካልሠራብህ፥
ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ።
31በግፈኛ ሰው አትቅና፥
መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ።
32ጠማማ ሁሉ በጌታ ፊት ርኩስ ነውና፥
ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው።
33የጌታ መርገም በክፉ ሰዎች ቤት ነው፥
የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል።
34 # ያዕ. 4፥6፤ 1ጴጥ. 5፥5። በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥
ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።
35ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፥
ሞኞች ግን መዋረድን ይቀበላሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in