YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘኍልቊ 11

11
እስራኤላውያን በምድረ በዳ ማጉረምረማቸው
1ሕዝቡም ስለ ደረሰባቸው መከራ በጌታ ላይ አጉረመረሙ፤ ጌታም ሰምቶ እጅግ ተቈጣ፤ የጌታም እሳት በመካከላቸው ነደደ፥ የሰፈሩንም ዳር በላ። 2ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ ጌታ ጸለየ፥ እሳቱም ጠፋ። 3የጌታም እሳት በመካከላቸው ስለ ነደደ የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው።
4በእነርሱም መካከል የነበረው የተለያየ ሕዝብ እጅግ ጐመጀ፤ የእስራኤልም ልጆች ዳግመኛ ዘወር በለው አለቀሱ እንዲህም አሉ፦ “የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? 5በግብጽ ሳለን እንዲያው በነጻ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ ሐብሐብውንም፥ ባሕሮውንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስታውሳለን፤ 6አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀ፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም የሚያው ነገር የለም።” 7#ዘፀ. 16፥31።መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፥ መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር። 8#ዘፀ. 16፥13-15።ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፥ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በሸክላም ድስት ይቀቅሉት ነበር፥ እንጐቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጐቻ ነበረ። 9ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በእርሱ ላይ ይወርድ ነበር።
10ሙሴም ሕዝቡ በየወገኑ፥ ሰው ሁሉ በየድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ የጌታም ቁጣ እጅግ ነደደ፤ ሙሴም በጣም ቅር ተሰኘ። 11ሙሴም ጌታን እንዲህ አለው፦ “ለምን በባርያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? 12አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር እንዳደርሳቸው፦ ‘ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንደምታቅፈው እንዲሁ በብብትህ እቀፋቸው’ የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? እነርሱንስ ወልጃቸዋለሁን? 13እነርሱም በፊቴ እያለቀሱ እንዲህ ይላሉና፦ ‘የምንበላውን ሥጋ ስጠን’፤ እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከወዴት አገኛለሁ? 14ለእኔ እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። 15እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ።”
ሰባው ሽማግሌዎች
16ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች እንደ ሆኑ የምታውቃቸውን የእስራኤል ሽማግሌዎች የሆኑ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፤ እነርሱንም ወደ መገናኛው ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር በየቦታቸው ይቁሙ። 17እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አኖረዋለሁ፤ አንተም ብቻህን እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። 18ሕዝቡንም እንዲህ በላቸው፦ ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ ምክንያቱም እንዲህ እያላችሁ ያለቀሳችሁት ለቅሶ ወደ ጌታ ጆሮ ደርሶአልና፦ ‘የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብጽ ሳለን በዚያ ደኅና ነበርን፤’ ስለዚህ ጌታ ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበላላችሁም። 19አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም ዐሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን ብቻ የምትበሉት አይደለም፤ 20ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን ጌታን ትታችሁታልና፥ በፊቱም፦ ‘ለምን ከዚያ ከግብጽ ወጣን?’ ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪ ወጣ እስኪያቅለሸልሻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።” 21ነገር ግን ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እኔ በመካከላቸው ሆኜ በእኔ ዘንድ ያሉት ሰዎች ሲቈጠሩ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ አልህ። 22እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድላቸውን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ እንዲያጠግባቸው ይሰበሰብላቸውን?” 23ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በውኑ ጌታ ለዚህ እጅ አጥሮት ነውን? አሁን ቃሌ ለአንተ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደሆነ አንተ ታያለህ።”
24ሙሴም ወጣ የጌታንም ቃላት ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። 25ጌታም በደመናው ውስጥ ሆኖ ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አኖረ፤ መንፈሱም በእነርሱ ላይ ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተናገሩም።
26ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈሩ ውስጥ ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ ሲሆን የሁለተኛው ስም ደግሞ ሞዳድ ይባል ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን ወጥተው አልሄዱም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። 27አንድ ጐልማሳ ሰው እየሮጠ መጥቶ፦ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈሩ ውስጥ ሆነው ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ብሎ ለሙሴ ነገረው። 28ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፦ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው” አለው። 29ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “የጌታ ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ ጌታም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያኖር፤ አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” 30ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።
ድርጭቶች
31ነፋስም ከጌታ ዘንድ ወጣ፥ ከባሕርም ድርጭቶችን አመጣ፥ እነርሱንም የአንድ ቀን መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ አጠገብ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ያህል ቈለላቸው። 32በዚያም ቀን ሁሉ በሌሊትም ሁሉ በማግስቱም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ ዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ የሚህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። 33ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳይታኘክ የጌታ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ ጌታም ሕዝቡን እጅግ ታላቅ በሆነ መቅሠፍት መታ። 34እንግዲህ የጐመጀውን ሕዝብ በዚያ ቀብረውታልና የዚያ ስፍራ ስም ኬብሮን-ሐታማ#11፥34 የምኞት መቃብር ማለት ነው። ተብሎ ተጠራ። 35ሕዝቡም ከኬብሮን-ሐታማ ወደ ሐጼሮት ተጓዙ በሐጼሮትም ተቀመጡ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in