የማርቆስ ወንጌል 3
3
ኢየሱስ እጀ ሰላላውን ሰው እንደ ፈወሰ
(ማቴ. 12፥9-14፤ ሉቃ. 6፥6-11)
1ኢየሱስ እንደገና ወደ ምኵራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ 2እነርሱም በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ አይተው ሊከስሱት ፈልገው ይጠባበቁት ነበር። 3እርሱም እጁ የሰለለችውን ሰው “ተነሥ! በመካከል ቁም” አለው። 4ከዚያም “በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዷልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ። 5ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ፥ ዙሪያውን በቁጣ ተመለከተና ሰውየውን፦ “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። እርሱም ዘረጋ፤ እጁም ዳነች። 6ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ተማከሩበት።
ሕዝቡ በባሕሩ አጠገብ እንደተሰበሰቡ
7ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላና ከይሁዳ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ 8ያደረገውን ነገር ሁሉ ሰምተው፥ ከኢየሩሳሌም፥ ከኤዶምያስ፥ ከዮርዳኖስ ማዶ፥ ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጡ። 9#ማር. 4፥1፤ ሉቃ. 5፥1-3።ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ እንዳያስጨንቁት ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ 10ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ በእጃቸው ሊነኩት ፈልገው ያጨናንቁት ነበር። 11ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” እያሉ ጮኹ። 12እርሱም ማንነቱን እንዳይገልጡ በጥብቅ ገሠጻቸው።
ስለ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መመረጥ
(ማቴ. 10፥1-4፤ ሉቃ. 6፥14-16)
13ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ። 14ከእርሱም ጋር እንዲሆኑና ለመስበክም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” አላቸው። 15አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። 16የተመረጡት ዐሥራ ሁለቱም፦ ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፤ 17ቦአኔርጌስ፥ ማለትም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሰየማቸው የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስን፤ 18እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርተሎሜውስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ቀነናዊው ስምዖን፥ 19እና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው።
የጸሐፍት ከንቱ ወሬ
(ማቴ. 12፥22-32፤ ሉቃ. 11፥14-23፤ 12፤ 10)
20ከዚያም ወደ ቤት ገቡ፤ ምግብ መመገብ እንኳ እስኪያቅታቸው ድረስ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። 21ዘመዶቹም “አእምሮውን ስቷል” ሲባል ሰምተው ሊይዙት መጡ። 22#ማቴ. 9፥34፤ 10፥25።ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጸሐፍትም#3፥22 የሕግ መምህራን። “በብዔልዜቡል ተይዟል! ደግሞም በዚህ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል!” ብለው ተናገሩ። 23እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን ሰይጣንን ሊያስወጣ እንዴት ይችላል? 24መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ 25እንዲሁም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤተሰብ ሊቆም አይችልም። 26ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ቢነሣና ቢለያይ መጨረሻው ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። 27ነገር ግን ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ አስቀድሞ ኀይለኛውን ሳያስር ንብረቱን መዝረፍ የሚችል የለም፤ ያንጊዜ ግን ቤቱን ይዘርፋል።
28“በእውነት እላችኋለሁ፤ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ፥ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ 29#ሉቃ. 12፥10።በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘለዓለም ጥፋት ይሆንበታል እንጂ ለዘለዓለም አይሰረይለትም።” 30ምክንያቱም “ርኩስ መንፈስ አለበት፤” ብለዋል።
ስለ ኢየሱስ እናት እና ስለ ወንድሞቹ
(ማቴ. 12፥46-50፤ ሉቃ. 8፥19-21)
31የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ ወደ እርሱ መጡ፤ በውጪም ቆመው ወደ እርሱ ሰው ላኩና አስጠሩት። 32ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና “እነሆ፥ እናትህ፥ ወንድሞችህና እኅቶችህ በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል፤” አሉት። 33እርሱም “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቃቸው። 34በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም እየተመለከተ፥ “እነሆ! እናቴና ወንድሞቼ! 35የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ፥ እኅቴም፥ እናቴም ነው” አለ።
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 3: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in