YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 2

2
ኢየሱስ አንድ ሽባ ሰው እንደ ፈወሰ
(ማቴ. 9፥1-8ሉቃ. 5፥17-26)
1ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ፤ በቤት ውስጥ እንዳለም ተሰማ። 2ሰዎች ከበሩ ውጭ ያለው ስፍራ እንኳን እስኪጠባቸው ድረስ ተሰበሰቡ፤ እርሱም ቃሉን ይነግራቸው ነበር። 3አራት ሰዎችም አንድ ሽባ ሰው ተሸክመው አመጡለት። 4ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ማቅረብ ስላልቻሉ፥ እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፤ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ። 5ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “አንተ ልጅ! ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል፤” አለው። 6በዚያም ተቀምጠው ከነበሩ አንዳንድ ጻሐፍት በልባቸውም “ይህ ሰው ስለምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? 7ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል፤” ብለው አሰቡ። 8ኢየሱስም በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ ወዲያው አውቆ እንዲህ አላቸው “በልባችሁ ይህን ስለምን ታስባላችሁ? 9ሽባውን ‘ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል፤’ ከማለትና ‘ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ፤’ ከማለት የቱ ይቀላል? 10ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” ብሎ ሽባውን፦ 11“አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። 12እርሱም ተነሥቶ ሁሉም እያዩት ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ስለዚህም ሰዎቹ ሁሉ ተደንቀው “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም፤” እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።
የሌዊ መጠራት
(ማቴ. 9፥9-13ሉቃ. 5፥27-32)
13ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። 14ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና “ተከተለኝ፤” አለው። ተነሥቶም ተከተለው።
15በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኀጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ፤ ይከተሉትም ነበር። 16ጸሐፍት ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ “ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድነው?” አሉ። 17ኢየሱስም ሰምቶ “ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም፤” አላቸው።
ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 9፥14-17ሉቃ. 5፥33-39)
18የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር። መጥተውም “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጾሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ስለ ምንድነው?” አሉት። 19ኢየሱስም አላቸው “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጾሙ አይችሉም። 20ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያ ወራትም ይጾማሉ። 21በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። 22በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል፤ የወይኑም ጠጅ ይፈሳል፤ አቁማዳውም ይጠፋል፤ አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ።”
ስለ ሰንበት የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 12፥1-8ሉቃ. 6፥1-5)
23 # ዘዳ. 23፥25። በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀመዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። 24ፈሪሳውያንም “እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለምን ያደርጋሉ?” አሉት። 25እርሱም “ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ 26#ዘሌ. 24፥9።#1ሳሙ. 21፥1-6።አብያታር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። 27ደግሞ “ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሯል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ 28እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው፤” አላቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in