YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 10

10
መፋታት እንደማይገባ
(ማቴ. 19፥1-12ሉቃ. 16፥18)
1ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ይሁዳ አገርና በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው አካባቢ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው።
2አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፥ “ሰው ሚስቱን መፍታት ይገባዋልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። 3እርሱም መልሶ፥ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው። 4#ዘዳ. 24፥1-4፤ ማቴ. 5፥31።እነርሱም፥ “ሙሴማ የፍች ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷአል” አሉ። 5ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው። 6#ዘፍ. 1፥27፤ 5፥2።ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። 7#ዘፍ. 2፥24።ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፤ 8ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ 9ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየውም።”
10እንደገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት። 11#ማቴ. 5፥32፤ 1ቆሮ. 7፥10፤11።እርሱም፥ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በእርሷ ላይ ያመነዝራል፤ 12እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው።
ኢየሱስ ሕፃናትን እንደ ባረከ
(ማቴ. 19፥13-15ሉቃ. 18፥15-17)
13ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፥ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። 14ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 15#ማቴ. 18፥3።እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” 16ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።
ስለ ሀብታሙ ወጣት
(ማቴ. 19፥16-30ሉቃ. 18፥18-30)
17ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፥ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ፥ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘለዓለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው። 18ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቸር የለም፤ 19#ዘፀ. 20፥13፤ ዘዳ. 5፥17፤ ዘፀ. 20፥14፤ ዘዳ. 5፥18፤ ዘፀ. 20፥15፤ ዘዳ. 5፥19፤ ዘፀ. 20፥16፤ ዘዳ. 5፥20፤ ዘፀ. 20፥12፤ ዘዳ. 5፥16።ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።” 20ሰውየውም፥ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው። 21ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላና፤ ተከተለኝም” አለው። 22ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ።
23ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፥ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው” አላቸው። 24ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው፤ 25ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል።” 26ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፥ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። 27ኢየሱስም አያቸውና፥ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው። 28ጴጥሮስም፥ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው። 29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፥ 30አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፥ ወንድሞችን፥ እኅቶችን፥ እናቶችን፥ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት የማይወርስ የለም። 31#ማቴ. 20፥16፤ ሉቃ. 13፥30።ነገር ግን ብዙዎች ፊተኞች የሆኑ ኋለኞች፥ ኋለኞች የሆኑም ፊተኞች ይሆናሉ።”
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለሦስትኛ ጊዜ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 20፥17-19ሉቃ. 18፥31-34)
32ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፥ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀመዛሙርቱ ተገረሙ፥ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤ 33እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ 34ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፥ ይገርፉታል፥ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”
የያዕቆብና የዮሐንስ ልመና
(ማቴ. 20፥20-28)
35ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት። 36እርሱም፥ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 37እነርሱም፥ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፥ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት። 38#ሉቃ. 12፥50።ኢየሱስም፥ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው። 39እነርሱም፥ “አዎን እንችላለን” አሉት። ኢየሱስም፥ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 40ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው። 41ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቆጣት ጀመሩ። 42#ሉቃ. 22፥25፤26።ኢየሱስም በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ አለቆች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፤ ሹሞቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ ታውቃላችሁ፤ 43#ማቴ. 23፥11፤ ማር. 9፥35፤ ሉቃ. 22፥26።በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ 44ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፥ የሁሉ ባርያ ይሁን፤ 45የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።”
ኢየሱስ ዐይነ ስውሩን በርጤሜዎስን እንደ ፈወሰ
(ማቴ. 20፥29-34ሉቃ. 18፥35-43)
46ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 47እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፥ “የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ” እያለ ይጮኽ ጀመር። 48ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፥ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ። 49ኢየሱስም ቆም ብሎ፥ “ጥሩት” አላቸው። እነርሱም ዐይነ ስውሩን፥ “አይዞህ፤ ተነሥ፤ ይጠራሃል” አሉት። 50እርሱም ልብሱን ጥሎ ብድግ በማለት፥ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ መጣ። 51ኢየሱስም፥ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው። ዐይነ ስውሩም፥ “መምህር ሆይ፤ እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው። 52ኢየሱስም፥ “ሂድ፥ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in