YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 20

20
የወይን አትክልት ሠራተኞች ምሳሌ
1“መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ የአትክልት ቦታ ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ትመስላለችና። 2ከሠራተኞቹ ጋር በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሰደዳቸው። 3ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈትተው የቆሙ ሌሎችን አየ፤ 4እነርሱንም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ፤’ አላቸው። 5እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። 6ወደ ዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ አላቸው። 7እነርሱም ‘የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው፤’ አሉት። እርሱም ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤’ አላቸው። 8#ዘሌ. 19፥13፤ ዘዳ. 24፥15።በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ ሹሙን ‘ሠራተኞቹን ጥራና ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ደመወዝ ስጣቸው፤’ አለው። 9ዐሥራ አንድ ሰዓት ላይ የገቡት መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 10መጀመሪያ የመጡትም በቀረቡ ጊዜ የበለጠ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 11በተቀበሉም ጊዜ በባለቤቱ ላይ አጉረመረሙ። 12እንዲህም አሉት ‘እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፤ የቀኑን ድካምና ሐሩር ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው።’ 13እርሱ ግን ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት ‘ወዳጄ ሆይ! አልበደልሁህም፤ ከእኔ ጋር በአንድ ዲናር አልተስማማህምን? 14የአንተ የሆነውን ውሰድና ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁህን ያህል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈለግሁ። 15የራሴ በሆነ ነገር ላይ የወደድሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንኩ ትመቀኛለህን? 16#ማቴ. 19፥30፤ ማር. 10፥31፤ ሉቃ. 13፥30።ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።’”
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለሦስተኛ ጊዜ እንደ ተናገረ
(ማር. 10፥32-34ሉቃ. 18፥31-34)
17ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ሳለ፥ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወሰዳቸው፥ በመንገድም ሳሉ እንዲህ አላቸው፦ 18“እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄድን ነው፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ተላልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ 19እንዲያላግጡበት፥ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።”
ስለ ዘብዴዎስ ልጆች
(ማር. 10፥35-45)
20በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ከልጆችዋ ጋር ወደ እርሱ ቀረበች። 21እርሱም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም “እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ እዘዝ” አለችው። 22ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” እነርሱም “እንችላለን” አሉት። 23እርሱም “ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ መስጠት የእኔ አይደለም ነገር ግን እርሱ በአባቴ ለተዘጋጀላቸው ነው፤” አላቸው። 24ዐሥሩም ይህንን በሰሙ ጊዜ በሁለቱም ወንድማማቾች ተቆጡ። 25#ሉቃ. 22፥25፤26።ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው “የአሕዛብ አለቆች ጌትነታቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታላላቆቹም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩአቸው ታውቃላችሁ። 26#ማቴ. 23፥11፤ ማር. 9፥35፤ ሉቃ. 22፥26።በእናንተ መካከል እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ከእናንተ መካከል ታላቅ መሆን የሚፈልግ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ 27ከእናንተም መካከል ፊተኛ መሆን የሚፈልግ የእናንተ ባርያ ይሁን፤ 28የሰው ልጅም ሊያገለግል፥ ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”
ኢየሱስ ሁለት ዐይነ ስውሮችን መፈወሱ
(ማር. 10፥46-52ሉቃ. 18፥35-43)
29ከኢያሪኮ ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። 30እነሆ፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንደሚያልፍ በሰሙ ጊዜ “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ ጮኹ። 31ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ፥ ጌታ ሆይ! ማረን” እያሉ አብዝተው ጮኹ። 32ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 33እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ ነው” አሉት። 34ኢየሱስም አዘነላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑ አዩ፥ ተከተሉትም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in