YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 2

2
የሰብአ ሰገል መምጣት
1ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፥ 2እንዲህም አሉ፦ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና።” 3ንጉሡ ሄሮድስ ሰምቶ ታወከ፤ መላዋ ኢየሩሳሌምም ከእርሱ ጋር ታወከች፤ 4ሊቃነ ካህናትንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። 5እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በይሁዳ ቤተልሔም ነው፤ በነቢዩ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤
6 # ሚክ. 5፥2። “በይሁዳ ምድር የምትገኚ አንቺ ቤተልሔም፥
ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤
ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መሪ ከአንቺ ይወጣልና።”
7ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ተረዳ። 8እንዲህ ብሎም ወደ ቤተልሔም ላካቸው፦ “ሂዱ፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” አላቸው። 9እነርሱም ንጉሡን ከሰሙ በኋላ ሄዱ፤ እነሆ፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። 10ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ በጣም ደስ አላቸው። 11ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ፥ ዕጣንና ከርቤ አቀረቡለት። 12ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ስላስጠነቀቃቸው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ።
ወደ ግብጽ ሽሽት
13እነርሱ ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሥ፥ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። 14እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤ 15#ሆሴዕ 11፥1።ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ፥ ይህም ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ነው።
ስለ ሕፃናት መገደል
16ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ወታደሮችን ልኮ ከሰብአ ሰገል በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን በቤተ ልሔምና በአካባቢዋ የነበሩትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። 17ያንጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ተፈጸመ፤
18 # ኤር. 31፥15። “የልቅሶና የብዙ ዋይታ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፤
ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤
የሉምና መጽናናትን እምቢ አለች።”
ከግብጽ መመለስ
19ሄሮድስ ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፤ 20እንዲህም አለው፦ “ተነሣ፤የሕፃኑን ነፍስ የሚፈልጉት ሞተዋልና ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ሂድ።” 21እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ። 22አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ፈንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልም ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ 23#ማር. 1፥24፤ ሉቃ. 2፥39፤ ዮሐ. 1፥45።በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው እንዲፈጸም፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in