YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ሚልክያስ 2

2
1“ካህናት ሆይ፥ አሁንም ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።
2“ባትሰሙ፥ ለስሜም ክብር ለመስጠት በልባችሁ ባታኖሩት፥” ይላል የሠራዊት ጌታ፥ “እርግማን እልክባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማለሁ፤ አሁንም ረግሜዋለሁ ምክንያቱም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና።”
3እነሆ፥ ዘራችሁን እገሥጻለሁ፥ በፊታችሁ ላይ ፈርስን እበትናለሁ፥ ይህም ፈርስ ለበዓላችሁ መሥዋዕት ካመጣችኋቸው ነው፤ እናንተንም ከእርሱ ጋር ያነሳችኋል#2፥3 ያስወግዳችኋል።
4 # ዘኍ. 3፥11-13። ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ለማድረግ ይህን ትእዛዝ እንደ ላክሁላችሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
5 # ዘኍ. 25፥12። ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና የሰላም ነበረ፤ እንዲያከብረኝ እነርሱን ሰጠሁት፤ እርሱም አከበረኝ፥ ከስሜም በማክበር ፈራኝ#2፥5 የአክብሮት ፍርሃት
6የእውነት ትምህርት በአፉ ውስጥ ነበረ፥ በከንፈሩም ውስጥ ስሕተት አልተገኘም፤ ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፥ ብዙዎችንም ከኃጢአት መለሰ።
7የካህን ከንፈሮች ዕውቀትን መጠበቅ አለባቸው፤ ሰዎችም ሕግን#2፥7 የሙሴ ሕግ (ቶራ) ከአፉ መፈለግ አለባቸው፤ ምክንያቱም የሠራዊት ጌታ መልእክተኛ ነው።
8እናንተ ግን ከመንገዱ ተለይታችኋል፤ በሕግም ብዙዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አፍርሳችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
9ስለዚህ መንገዴን ስላልጠበቃችሁ፥ በሕግም ለሰው ፊት እንዳዳላችሁ መጠን፥ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ አድርጌአችኋለሁ።
ቃል ኪዳኑ በይሁዳ ረከሰ
10የሁላችን አባት አንድ አይደለምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማርከስ ሁላችንም ለምን ወንድማችንን እናታልላለን?
11ይሁዳ አታልሎአል፥ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ውስጥ ርኩሰት ሠርቷል፤ ይሁዳ ጌታ የወደደውን መቅደስ አርክሶአል፥ የባዕድንም አምላክ ልጅ አግብቶአል።
12ይህን ከሚያደርግ ሰው፥ የሚጠራውንና የሚመልሰውን ለሠራዊትም ጌታ ቁርባን የሚያቀርበውን ከያዕቆብ ድንኳን ያጠፋል።
13ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል፤ እግዚአብሔር ቁርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በልቅሶ በኅዘንም ትከድናላችሁ።
14እናንተም፦ ለምን ይህ ሆነ? ትላላችሁ። ምክንያቱም ሚስትህን አታልለሃታልና ጌታ በአንተና በልጅነት#2፥14 በወጣትነት። ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው፤ እርሷም ጓደኛህና የቃል ኪዳን ሚስትህ ነበረች።
15አንድ አላደረጋቸውምን? የመንፈስም ቅሪት ለእርሱ ነው? አንዱስ ምን ፈልጎ ነው? የእግዚአብሔርን ዘር ፈልጎ ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል።
16መፋታትን እጠላለሁና፥ ይላል ጌታ የእስራኤል አምላክ፥ ልብሱንም በሁከት የሚሸፍንን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ።
17በቃላችሁ ጌታን አሰልችታችሁታል። እናንተም፦ እርሱን ያሰለቸነው በምንድን ነው? ትላላችሁ። “ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በጌታ ፊት መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል” ወይም “የፍትሕ አምላክ የት አለ?” በማለታችሁ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for ትንቢተ ሚልክያስ 2