YouVersion Logo
Search Icon

የዮሐንስ ወንጌል 3

3
ኢየሱስና ኒቆዲሞስ
1ከፈሪሳውያንም ወገን አንድ ሰው ነበረ፤ ስሙ ኒቆዲሞስ ሲሆን የአይሁድም አለቃ ነበረ፤ 2እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ “መምህር ሆይ! ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር መሆንህን እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በስተቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል ማንም የለምና፤” አለው። 3ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም፤” አለው። 4ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ መወለድ ይችላልን?” አለው። 5ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም። 6ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። 7ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ። 8ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” 9ኒቆዲሞስ መልሶ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለው። 10ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህንን አታውቅምን? 11እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ የእኛንም ምስክርነት አትቀበሉትም። 12#ጥበ. 9፥16፤17።ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13#ባሮክ 3፥29።ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፤ እርሱም የሰው ልጅ ነው። 14#ዘኍ. 21፥9፤ ጥበ. 16፥5-7።ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ የሰው ልጅም መሰቀል ይገባዋል። 15በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ።
16“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። 17ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። 18በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ ከወዲሁ ተፈርዶበታል። 19ፍርዱም ይህ ነው፥ ብርሃንም ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። 20ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ 21እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር መከናወኑ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”
የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት
22ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፤ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር። 23ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን፥ በዚያ ብዙ ውሃ ነበርና፥ ያጠምቅ ነበር፤ እየመጡም ይጠመቁ ነበር፤ 24#ማቴ. 14፥3፤ ማር. 6፥17፤ ሉቃ. 3፥19፤20።ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልወረደም ነበርና።
25በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከልም ስለ ማንጻት ሥርዓት ክርክር ተነሣ። 26ወደ ዮሐንስም መጥተው “መምህር ሆይ! በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል፤ ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ፤” አሉት። 27ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሰው ከሰማይ ካልተሰጠው እንዳችም ነገር ሊቀበል አይችልም። 28#ዮሐ. 1፥20።እናንተ ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ፤’ እንዳልሁ እራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። 29ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። 30እርሱ እንዲልቅ እኔ ግን እንዳንስ ያስፈልጋል።”
31ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው፥ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። 32ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፤ ምስክርነቱንም የሚቀበለው የለም። 33ምስክርነቱን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደሆነ አረጋገጠ። 34እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና። 35#ማቴ. 11፥27፤ ሉቃ. 10፥22።አባት ልጁን ይወዳል፥ ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል። 36በልጁ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ለልጁ የማይታዘዝ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in