YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 17

17
የይሁዳ ኃጢአትና ቅጣት
1“የይሁዳ ኃጢአት በብረት ብዕር ተጽፎአል፤ በተሾለም ዕብነ አልማዝ በልባቸው ጽላትና በመሠዊያዎቻችሁ ቀንዶች ተቀርጾአል። 2ልጆቻቸውም ከለመለሙ ዛፎች በታችና በረዘሙት ኮረብቶች ላይ ያሉትን መሠዊያዎቻቸውንና የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውን ያስታውሳሉ። 3በሜዳ ያለው ተራራዬ ሆይ! ባለጠግነትህንና መዝገቦችህን ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችህም ስለ ኃጢአት በድንበሮችህ ሁሉ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣለሁ። 4አንተም የሰጠሁህን ርስት ትለቅቃለህ፥ በማታውቃትም ምድር ለጠላቶችህ ባርያ እንድትሆን አደርግሃለሁ፤ ለዘለዓለም የሚነድደውን እሳት በቁጣዬ አንድዳችኋልና።”
5ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ፥ ልቡም ከጌታ የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። 6እርሱ በምድረ በዳ እንዳለ ቁጥቋጦ ነው፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በማይቀመጥበት፥ ጨው ባለበት ምድር፥ በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል። 7በጌታ የታመነ ጌታም መተማመኛው የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። 8#መዝ. 1፥3።በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሮቹን እንደሚዘረጋ፥ ሙቀትም በመጣ ጊዜ እንደማይፈራ፥ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም ከማፍራት እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።”
9የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል? 10#ራእ. 2፥23፤ መዝ. 62፥12።“እኔ ጌታ ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት ልብን እመረምራለሁ ኩላሊትንም እፈትናለሁ።” 11ያልወለደችውን እንደምታቅፍ ቆቅ፥ ባለጠግነትንም በቅን ባልሆነ መንገድ የሚሰበስብ ሰው እንዲሁ ነውና፤ በእኩሌታ ዘመኑ ይተወዋል፥ በፍጻሜውም ሰነፍ ይሆናል።
12የመቅደሳችን ስፍራ ከጥንት ጀምሮ ከፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው። 13የእስራኤል ተስፋ አቤቱ! የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ ጌታን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋሉ።
ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ፍርድ መጸለዩ
14አቤቱ! ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና። 15እነሆ፦ “የጌታ ቃል ወዴት አለች? አሁን ትምጣ!” ይሉኛል። 16እኔም አንተን ተከትዬ እረኛ ከመሆን አልቸኰልሁም፥ የመከራንም ቀን አልወደድሁም፤ አንተ ታውቃለህ፤ ከከንፈሬ የወጣው በፊትህ ነበረ። 17ለማስፈራራት አትሁንብኝ፤ በመከራ ቀን አንተ መጠጊያዬ ነህ። 18አሳዳጆቼ ይፈሩ፥ እኔ ግን አልፈር፤ እነርሱ ይደንግጡ፥ እኔ ግን አልደንግጥ፤ ክፉንም ቀን አምጣባቸው፥ በሁለት እጥፍ ጥፋት አጥፋቸው።
የሰንበትን ቀን መቀደስ
19ጌታ እንዲህ ይለኛል፦ “ሂድ፥ የይሁዳም ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ ልጆች በር፥ በኢየሩሳሌምም በሮች ሁሉ ቁም፤ 20እንዲህም በላቸው፦ ‘በእነዚህ በሮች የምትገቡ፥ የይሁዳ ነገሥታት ሆይ! ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ የጌታን ቃል ስሙ። 21#ነህ. 13፥15-22።ጌታ እንዲህ ይላል፦ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፥ በሰንበትም ቀን ሸክም አትሸከሙ፥ በኢየሩሳሌምም በሮች አታስገቡ፥ 22#ዘፀ. 20፥8-10፤ ዘዳ. 5፥12-14።ከቤቶቻችሁም በሰንበት ቀን ሸክምን አታውጡ፥ ሥራንም ሁሉ አትሥሩበት፤ አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁ የሰንበትን ቀን ቀድሱ። 23እነርሱ ግን አልሰሙም ጆሮአቸውን አላዘነበሉም፥ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም አንገታቸውን አደነደኑ።
24“ ‘እኔን ፈጽሞ ብትሰሙ፥ ይላል ጌታ፥ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ባታስገቡ፥ የሰንበትንም ቀን ብትቀድሱ ሥራንም ሁሉ ባትሠሩበት፥ 25በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መሳፍንት፥ በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ እየተቀመጡ በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ እነርሱና መሳፍንቶቻቸው የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚቀመጡ ይገባሉ፥ ይህችም ከተማ ለዘለዓለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች። 26የሚቃጠለው መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን፥ የእህሉንም ቁርባን ዕጣኑንም፥ የምስጋናውንም መሥዋዕት ይዘው ከይሁዳ ከተሞች ከኢየሩሳሌምም ዙሪያ፥ ከብንያምም አገር፥ ከቈላውም ከደጋውም ከደቡብም ወደ ጌታ ቤት ይመጣሉ። 27ነገር ግን የሰንበትን ቀን እንድትቀድሱ፥ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፥ በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች፥ አትጠፋምም።’ ”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ትንቢተ ኤርምያስ 17