YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኤርምያስ 13

13
የበፍታው መታጠቅያ
1ጌታ እንዲህ ይለኛል፦ “ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራን መታጠቂያ ለእራስህ ግዛ፥ ወገብህንም ታጠቀው፤ በውኃም ውስጥ አትንከረው።” 2እንደ ጌታም ቃል መታጠቂያን ገዛሁ ወገቤንም ታጠቅሁት። 3የጌታ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እኔ መጣ 4እንዲህም አለኝ፦ “የገዛኸውን በወገብህ ያለውን መታጠቂያ ወስድ፥ ተነሣም፥ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፥ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት።” 5ጌታም እንዳዘዘኝ ሄድሁ በኤፍራጥስም አጠገብ ሸሸግሁት። 6ከብዙ ቀንም በኋላ ጌታ፦ “ተነሣ፥ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም እንድትሸሽገው ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ” አለኝ። 7እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄድሁ ቆፈርሁም፥ ከዚያ ከሸሸግሁበትም ስፍራ መታጠቂያውን ወሰድሁ። እነሆም፥ መታጠቂያው ተበላሽቶ ነበር፥ ለምንም አይረባም።
8የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9“ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አጠፋለሁ። 10ቃሌን ለመስማት እንቢ የሚሉ፥ በልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ሊያገለግሉአቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ፥ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንደማይረባ እንደዚህ መታጠቂያ ይሆናሉ። 11መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደሚጣበቅ፥ እንዲሁ ሕዝብና ስም፥ ምስጋናና ክብር እንዲሆኑልኝ የእስራኤልን ቤት ሁሉ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ነገር ግን አልሰሙም።”
የወይን ጠጅ ማድጋው ምሳሌ
12ስለዚህ፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል” ብለህ ይህን ቃል ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱም፦ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንደሚሞላ በእርግጥ እኛ አናውቅምን?” ይሉሃል። 13አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት ካህናቱንም ነቢያቱንም በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። 14ሰውንም ከሰው ጋር፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ፥ አላትማቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራም፥ አላዝንም፥ አልምርም።”
ምርኮ አይቀሬ መሆኑ
15ስሙ፥ አድምጡም፤ ጌታ ተናግሮአልና አትታበዩ። 16ሳትጨልም እግራችሁም በጨለሙት ተራሮች ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨልማ ሳይለውጠው፥ ለአምላካችሁ ለጌታ ክብርን ስጡ። 17ይህን ባትሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፤ የጌታም መንጋ ተማርኮአልና ዓይኔ እጅግ ታነባለች፥ እንባንም ታፈስሳለች።
18ለንጉሡና#13፥18 የንጉሡ ስም ዮአኪን ሲሆን በሁለተኛ ነገሥት 24፥8 ላይ ተገጾ ይገኛል። ለንጉሥ እናት ለእቴጌይቱ#13፥18 እናቱም ኔስታ ትባል ነበር። ይህም በሁለተኛ ነገሥት 24፥8 ላይ ተገጾ ይገኛል።፦ “የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ተዋርዳችሁ ተቀመጡ” በል። 19የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፥ የሚከፍታቸውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተማርኮአል፥ ፈጽሞ ተማርኮአል።
20“ዓይናችሁን አንሥታችሁ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቱ፤ ለአንቺ የተሰጠ መንጋ፥ የተዋበ መንጋሽ፥ ወዴት አለ? 21ወዳጆችሽ እንዲሆኑ ያስተማርሻቸውን በራስሽ ላይ አለቆች ባደረጋቸው ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን? 22በልብሽም፦ ‘እነዚህ ነገሮች ስለምን ደረሱብኝ?’ ብትዪ፥ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሣ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፎአል። 23በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ ይችላልን? እናንተ ክፋትን የለመዳችሁ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ። 24ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ። 25ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽ፥ የለካሁልሽም ድርሻሽ ይህ ነው፥ ይላል ጌታ። 26ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል። 27አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የአመንዝራነትሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ፥ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው?”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in