ወደ ገላትያ ሰዎች 6
6
የባልንጀራን ሸክም ስለ መሸከም
1ወንድሞች ሆይ! ሰው ማንኛውንም ኃጢአት አድርጎ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ዓይነቱን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። 2የእርስ በርሳችሁን ሸክም ተሸከሙ፥ በዚህም የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ። 3አንድ ሰው ምንም ሳይሆን አንድ ነገር#6፥3 ከሌሎቹ የተሻለ ቢመስለው። የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። 4እያንዳንዱ የገዛ ሥራውን ይፈትን፤ ከዚያም በኋላ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፥ ስለ ሌላው ግን አይደለም። 5እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ይሸከማልና።
6ቃሉን የሚማር መልካሙን ነገር ሁሉ ከሚያስተምረው ጋር ይካፈል።
7አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና። 8ምክንያቱም ወደ ገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፥ በመንፈስ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘለዓለምን ሕይወት ያጭዳል። 9መልካምን ሥራ ለመሥራት አንታክት፥ ካልዛልን ወቅቱ በደረሰ ጊዜ እናጭዳለንና። 10ስለዚህ ጊዜ ሳለን ለሰው ሁሉ፥ በተለይም ለእምነት ቤተሰቦች መልካም እናድርግ።
የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ
11እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። 12በሥጋ መልካም ሆነው መታየት የሚፈልጉ ሁሉ እንድትገረዙ አስገደዱአችሁ፤ ይህን ያደረጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። 13የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም፥ ነገር ግን በሥጋችሁ እንዲመኩ እንድትገረዙ ይፈልጋሉ። 14ለእኔ ግን፥ ዓለም ለእኔ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት አይሁንብኝ። 15አዲስ ፍጥረት መሆን እንጂ፥ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። 16በዚህ ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ እና በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።
17እኔ የኢየሱስን ምልክት በሰውነቴ ላይ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ።
18ወንድሞች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
Currently Selected:
ወደ ገላትያ ሰዎች 6: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in