YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መክብብ 5

5
1እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትቸኩል፥ ልብህም በእግዚአብሔር ፊት ቃልን ለመናገር አይቸኩል፥ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። 2ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል፥ እንዲሁም የአላዋቂም ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል። 3#መዝ. 65፥13፤14።አላዋቂዎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፥ የተሳልኸውን ፈጽመው። 4ተስለህ ካለመፈጸም ባትሳል ይሻላል። 5አፍህ ወደ ኃጢአት እንዲወስድህ አትፍቀድለት፥ በመልአክም ፊት፦ ስሕተት ነበረ አትበል፥ እግዚአብሔር በቃልህ ለምን ይቈጣ? ለምንስ የእጅህንም ሥራ ያጥፋ? 6ብዙ ሕልም ባለበት፥ እንዲሁም ብዙ ቃል ባለበት፥ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፥ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ።
7ከፍ ካለው ባለ ሥልጣን በላይ ሌላ ከፍ ያለ ይመለከታልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በአገሩ ድሆች ሲገፉ፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አትደነቅ። 8በጠቅላላው ይህ ለአገሩ ይጠቅማል፤ ንጉሥም ከእርሻ ይጠቀማል።
9ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፥ ሀብትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 10ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፥ ሀብቱን በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? 11ጥቂትም በላ ብዙ፥ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የሀብታም ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።
12ከፀሐይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፥ ራስን ለመጉዳት#5፥12 በተቀመጠው ሀብት ምክንያት የሚከሰተውን ጭንቀትና ሐሳብ ለማመልከት ነው። በባለቤቱ ዘንድ የተቀመጠ ሀብት። 13ያችም ሀብት በክፉ ነገር ትጠፋለች፥ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም። 14#ኢዮብ 1፥21፤ 1ጢሞ. 6፥7።ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፥ ከጥረቱም በእጁ ሊወስደው የሚችለው ምንም ነገር የለም። 15ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ነው፥ እንደመጣ እንዲሁ ይሄዳል፥ ድካሙም ለነፋስ ከሆነ ጥቅሙ ምንድነው? 16ዘመኑን በሙሉ በጨለማ፥ በከባድ ብስጭት፥ በደዌና በቁጣ ይጨርሳል።
17እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ቢኖር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሲበላና ሲጠጣ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ሲለው ነው፥ ይህ እድል ፈንታው ነውና። 18እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ሀብትና ንብረት መስጠቱ፥ ከእርሷም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ሥልጣን መስጠቱ ነው፥ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 19እግዚአብሔር በልቡ ደስታን እስካኖረ ድረስ፥ እርሱ የሕይወቱን ዘመን እጅግም አያስብም#5፥19 የሚጨነቅበትም ጊዜ የለውም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in