YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ መግቢያ

መግቢያ
የሐዋርያት ሥራ ከሉቃስ ወንጌል የቀጠለ ነው፤ የመጽሐፉ ዋና ዓላማ የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ስለ እርሱ የሚናገረውን የምሥራች ቃል “በኢየሩሳሌም፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ፥ በሰማርያ፥ እስከ ምድርም ዳርቻ” (1፥8) እንዴት እንዳሠራጩ መተረክ ነው፤ መጽሐፉ የክርስትና እምነት በአይሁድ መካከል ተጀምሮ የመላው ዓለም ሕዝብ እምነት እስኪሆን ድረስ እንዴት እንደ ተስፋፋ የሚናገር ታሪክ ነው። ክርስቲያኖች የሮምን መንግሥት ለመቀናቀን ውስጥ ለውስጥ የሚሠሩ ሰዎች እንዳልሆኑና የክርስትና ሃይማኖት በአይሁድ ሃይማኖት የተሰጡት ተስፋዎች እንዴት ፍጻሜ እንዳገኙ የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው።
የሐዋርያት ሥራ ስለ ኢየሱስ የሚነገረው የምሥራች ቃል የሚደርስበት ቦታ በየጊዜው እየሰፋ መሄዱን ያሳያል፤ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያንን መመሥረት በሚያንጸባርቁ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ሊመደብ ይችላል፦
1. የክርስትና ሃይማኖት ከኢየሱስ ዕርገት በኋላ በኢየሩሳሌም ስለ መጀመሩ፤
2. በእስራኤል አገር በሙሉ ስለ መዳረሱ፤
3. ሮምን ጨምሮ በሜዲቴራኒያን ባሕር ዙሪያ ባሉት አገሮች ስለ መስፋፋቱ።
በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ጐላ ብሎ የሚታየው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ሲሆን በጰንጠቆስጤ ቀን በኢየሩሳሌም በነበሩት አማኞች ላይ በኃይል መውረዱን፥ እንዲሁም በመጽሐፉ ውስጥ በተዘረዘሩት ድርጊቶች ሁሉ እንደታየው መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንንና መሪዎችዋን መምራቱንና ማበረታታቱን ይገልጻል። በጥንት ጊዜ ይቀርብ የነበረው የክርስትና መልእክት በልዩ ልዩ ስብከቶች ውስጥ፥ በአስተዋጽዖ መልክ ቀርቦአል፤ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተፈጸሙት ድርጊቶችም መልእክቱ በአማኞች ሕይወትና በቤተ ክርስቲያን ኅብረት የነበረው ኃይል ምን ያኽል ታላቅ እንደነበር ያስረዳሉ።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
የምስክርነቱ ዝግጅት (1፥1-26)
ኢየሱስ በመጨረሻ የሰጠው ትእዛዝና ተስፋ (1፥1-14)
በይሁዳ ቦታ የተተካ (1፥15-26)
ምስክርነት በኢየሩሳሌም (2፥1—8፥3)
ምስክርነት በይሁዳና በሰማርያ (8፥4—12፥25)
የጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት (13፥1—28፥31)
የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞ (13፥1—14፥28)
የኢየሩሳሌም ጉባኤ (15፥1-35)
ሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ (15፥36—18፥22)
ሦስተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ (18፥23—21፥16)
የጳውሎስ በኢየሩሳሌም፥ በቂሳርያና በሮም መታሰር (21፥17—28፥31)
ምዕራፍ

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in